ኢሳት (ኅዳር 29 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የሚገኘው የደቡብ ሱዳን ተማሪዎች ህብረት በሃገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ በሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ሊያካሄድ የነበረውን የተማሪዎች ተወካዮች ምርጫ አራዘመ።
ከ35ሺ የሚበልጡ የደቡብ ሱዳን ተማሪዎች በኢትዮጵያ የተያያዩ ዩኒቨስቲዎች የከፍተኛ ትምህርትን በመከታተል ላይ ሲሆኑ፣ የተማሪዎቹ ህብረት ከአንድ ሳምንት በኋላ አዳዲስ የተማሪዎች ተወካዮችን ለመምረጥ ፕሮግራም ይዞ እንደነበር ታውቋል።
ይሁንና በኢትዮጵያ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህዝባዊ ስብሰባዎችን የሚከለከል በመሆኑ የተማሪዎቹ ህብረት ምርጫውን በተያዘው ፕሮግራም መሰረት እንዳማያከናውን መግለጹን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ሃሙስ ዘግቧል።
የተማሪዎቹ ህብረት ሃላፊ የሆኑት ጀምስ ዮኦት ተማሪዎቹ በኢትዮጵያ የታወጀውን አዋጅ ግምት ውስጥ በማስገባት የተማሪዎቹ ምርጫ መተላለፉን በበጎ መልክ እንዲቀበሉት አሳስበዋል።
ከሰባት አመት በፊት የተመሰረተው የደቡብ ሱዳን ተማሪዎች ህብረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተጠናቀቀ በኋላ ምርጫውን እንደሚያካሄድና በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ምርጫው በትዕግስት እንዲጠብቁ ጠይቋል።
ይኸው በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ ዋጅ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አለም አቀፍ ተቋማት የተለያዩ ህዝባዊ ስብሰባዎችን እና መሰል ዝግጅቶችን እንዲያከናውኑ ማድረጉንም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ የመለክታል።
በርካታ የአውሮፓ ሃገራት የአዋጁ መውጣትን ተከትሎ ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ ዕርምጃን እንዲወስዱ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።
ከፈረንጆቹ አመት አዲስ አመት ጋር በተገናኘ ወደ ኢትዮጵያ ሊጓዙ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ አለም አቀፍ ቱሪስቶች ጉዞአቸውን እንዲሰርዙ ዘጋርዲያን ጋዜጣ የጉዞ ወኪሎችን ዋቢ በማድረግ ሰሞኑን መዘገቡ የሚታወስ ነው።