በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን አፈና ተጠናክሮ እንደቀጠለ አንድ አለም አቀፍ ተቋም ገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 21 ፣ 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት በሃገር ውስጥ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ አለም አቀፍ ትኩረትን እንዲያገኝ ለማድረግ ከውጭ ሃገር የሚሰራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ የቁጥጥር ዘመቻ መክፈቱን ግሎባል ቦይስ የተሰኘ አለም አቀፍ ተቋም ይፋ አደረገ።

በዚሁ የመንግስት ዘመቻም በ10 ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ተከታታይ ያለው ኢሳት እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ስርጭት መስተጓጎሉን በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ የሚሰራው ተቋም አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመወን ግድያ የሚያወግዙና አጋርነትን የሚያሳዩ ዘፈኖችም ለህዝብ እንዳይቀርቡ እገዳ እንደተጣለባቸው ግሎባል ቮይስ የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ይፋ ባደረገው ረፖርት ገልጿል።

ይኸው በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግም የሳተላይት ዲሾች በመንግስት ልዩ ትዕዛዝ እንዲወገዱ እንቅስቃሴ መደረጉንም አለም አቀፍ ድርጅቱ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ ሃገር የሚተላለፉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ከመቆጣጠሩ በተጨማሪ በተቃዋሚ አመራሮችና አባላት ላይ እንዲሁም በጋዜጠኞች ላይ የእስር ዘመቻን ከፍቶ እንደሚገኝም ግሎባል ቮይስ አስታውቋል።

የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ስርጭት ለማወክ ጎን ለጎን የተቃዋሚ ሃይሎች ተብለው የተፈረጁ ዌብሳይቶችንና የዲጂታል ራዲዮ ስርጭቶችም ቁጥጥር እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በሃገር ውስጥ በሚሰራጭ የግል ኤፍኤም ጣቢያዎች ላይ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ማረጋገጡ የሚታወስ ሲሆን በተለይ በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ሽፋን እንዲያገኝ እገዳ መጣሉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

በእነዚሁ ጣቢያዎች የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ዘፈኖችና ሌሎች የኦሮምኛ የኪነ-ጥበብ ስራዎች እንዳይተላለፉ ማዕቀብ ተጥሎባቸው እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።

ሂውማን ራይትስ ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግስት ሰላማዊ ጥያቄን በሚያቀርቡ አካላት ላይ የሚወስደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ግድያን የፈጸሙ አካላትም ለፍትህ እንዲቀርቡ አሳስበዋል።