በኢትዮጵያ የመኪና አደጋ ከፍተኛ ገዳይ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ

መስከረም ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመኪና አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ የሰዎችን ሕይወት ቀጣፊ ከሆነባቸው አገራት ተርታ ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ አገር መሆኗን የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በሪፖርቱ ገልጿል።ድርጅቱ ከመቶ ሺህ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 3 ሺ 874 ሰዎች ለሞት እንደሚጋለጡና 80 % የሚሆነው የአደጋው ምንጭ የአሽከርካሪዎች ጥፋት ሲሆን፣ የተቀረው 20 በመቶ ደግሞ በመንገድ ችግሮች መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።
ባለፈው ዓመት ብቻ ከ17 ሺ 052 በላይ የተሽከርካሪ አደጋ ተከስትዋል። አምና ብቻ በመኪና አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር 418 ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺ 676 የሚሆኑት ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስባቸው ፣ 194 ሚሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ውድመትም ደርሷል።
ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር ኢትዮጵያ በመኪና አደጋ ሳቢያ የሰው ሕይወት ከሚጠፋባቸውና የንብረት ውድመት ከሚደርስባቸው አገራት መካከል ቀዳሚዋ አገር ተብላለች።