(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 26/2009) ኢትዮጵያ ያለባት እዳ 40 ቢሊየን ዶላር በደረሰበት በአሁኑ ወቅት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከተለያዩ ዓለምዓቀፍ አበዳሪዎች የወሰዱት ብድር የመመለሺያ ጊዜው በመድረሱ መንግስት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መወደቁ ተሰማ።
ሐገሪቱ በወጭ ንግድ የምታገኘው ገንዘብ ከአመት አመት እየቀነሰ በቀጠለበትና 3 ቢሊየን ዶላር ማድረስ ባልተቻለበት ሁኔታ መንግስት በዚህ አመት የሚጠበቅበትን የ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር መክፈል የሚችልበት አማራጭ እንደሌለውም የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።
የ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር እዳውን መክፈል ጣር የሆነበት የሕወሃት መንግስት በአሁኑ ሰአት ከሱዳን ለመግዛት ያሰበውን ነዳጅ እንኳን በዱቤ እንዲሰጡት የተለያዩ መለማመጫዎችን በማቅረብ ላይ መሆኑንም የኢሳት ምንጮች አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ያለባት እዳ 40 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከተለያዩ ዓለምዓቀፍ አበዳሪዎች የወሰዱት ብድር የመመለሺያ ጊዜው ደግሞ ቀኑን ቆጥሮ መድረሱን መረጃዎች አመልክተዋል።
በሕወሃት የሚመራው መንግስትም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ወድቋል ይላሉ የኢሳት ምንጮች።
ሐገሪቱ በወጭ ንግድ የምታገኘውን ገንዘብ 3 ቢሊየን ዶላር ማድረስ ጭንቅ ሆኖባታል።ይህ ባለበት ሁኔታም መንግስት በዚህ አመት የሚጠበቅበትን የ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር መክፈል የሚችልበት አማራጭ እንደሌለውም የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።
የ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር እዳውን መክፈል ጣር የሆነበት የሕወሃት መንግስት በአሁኑ ሰአት ከሱዳን ለመግዛት ያሰበውን ነዳጅ እንኳን በዱቤ እንዲሰጡት የተለያዩ መለማመጫዎችን በማቅረብ ላይ መሆኑን ታውቋል።
ከገባበት ውጥረት ለመውጣትም በቀድሞ መንግስታት የተሰሩ አትራፊ ድርጅቶችን ለመሸጥ ሳይገደድ እንደማይቀር ተመልክቷል።
ፌደራል መንግስቱ የተበደረው የ30 ቢሊየን ዶላር የረዥም ግዜ ብድር መሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በዚህ ረገድ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተደቀነ ችግር አለመኖሩን የሚገልጹት ምንጮች ለመንግስት የልማት ድርጅቶች የተወሰደው የ10 ቢሊየን ዶላር ብድር ግን በ8 አመት ውስጥ የሚከፈል መሆኑን ይናገራሉ።
ታዲያ በዚህ አመት የሚመለሰው የብድር መጠን 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ሲሆን ከነ ወለዱ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር መሆኑንም መረዳት ተችሏል።
አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ባስቀመጠው መመዘኛ ሀገራት በትንሹ የ3 ወር ተጠባባቂ የውጭ ምንዛሪ እንዲኖራቸው የሚጠበቅ ቢሆንም በኢትዮጵያ ያለው ተጠባባቂ የውጭ ምንዛሪ ግን የ6 ሳምንት ብቻ ነው።
ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ባለስልጣን፣ለስኳር ኮርፖሬሽን፣ለመንገዶች ባለስልጣን፣ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ለኢትዮ ቴሌኮም እንዲሁም ለኢትዮጵያ ባቡር ድርጅት መንግስት ከወሰደው ብድር በዚህ አመት የሚመለሰው 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ነው።
በቀጠዩ አመት እየጨመረ እንደሚሄድም መረዳት ተችሏል።
ለልማት ድርጅቶቹ የተወሰደው ብድር ተቋማቱ መልሰው ይከፍላሉ በሚል ቢሆንም ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከኢትዮ ቴሌኮም ውጭ ያሉት እንኳን ብድሩን ሊመልሱ የሰራተኞቻቸው ደሞዝ የሚሸፈነው በፌደራል መንግስት እንደሆነ ታውቋል።
በአጠቃላይ ባለው በዚህ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር እንዲሁም እዳ መክፈያው ጊዜ በመቃረቡ መንግስት ነዳጅ ለማስገባትም አቅም እያነሰው በመገኘቱ ነዳጅ ከሱዳን በዱቤ ማግኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተደራደረ መሆኑ ተሰምቷል።
በዚህም የተነሳ ዋናው የወጭ ንግድ መስመር ተብሎ ከ4 ቢሊየን ዶላር በላይ የባቡር ሀዲድ የተዘረጋበት የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ተመርቆ ሁለት አመት ሳይሞላው ኢትዮጵያ በዋናነት የሱዳን ወደብን ለመጠቀም እንደወሰነች ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
ሱዳን ነዳጅን በብድር ስትሰጥ ኢትዮጵያ ደግሞ የሱዳንን ወደብ በዋናነት በክፍያ ለመጠቀም እንደወሰነች በሌላም በኩል ከድንበር ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር በኢትዮጵያ ኪሳራ ለመፍታት ሳይሞከር እንዳልቀረ የውስጥ ምንጮች ጠቁመዋል።
አወዛጋቢው የኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር ለ10 አመታት በአደራ በሱዳን ይዞታ ስር እንዲቀጥል ስምምነት ላይ የተደረሰው ሱዳን ነዳጅ በዱቤ እንድትሰጥ የቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ነው።
በአጠቃላይ ሀገሪቱ የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ ቀውስ ተከትሎ ብሔራዊ ባንክና ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር እርስ በርስ እየተወጃጀሉ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
በሀገር ውስጥ በመንግስት መዋቅርም ሆነ ከመንግስት ውጭ የሆኑ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ብድሩ አሳሳቢ ችግር እንደሚደቅን በወቅቱ አስጠንቅቀው እንደነበር የሚገልጹት ምንጮች ማክሮ ኢኮኖሚው የተረጋጋ ስለሆነ ብድሩን መመለስ እንችላለን በማለት ብድሩን ሲያበረታቱ የነበሩት የብሔራዊ ባንክና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባለስልጣናት እንደነበሩ አመልክተዋል።
እነዚህ ወገኖች ሁለቱም በጉዳዩ ተጠያቂ ሆነው ሳለ መወነጃጀላቸው ከሃላፊነት ሽሽት ነው ሲሉም ይገልጻሉ።
ሐገሪቱ ከፍተኛ እዳ ውስጥ ተዘፍቃ ብድሩን መመለስ ብትቸገርም በብድሩ ሒደትና ከብድሩ በኋላ በቀጠሉ ስራዎች የምድር ባቡር ሊቀመንበር እንዲሁም የኢንደስትሪ ፓርክ አስተባባሪው ዶክተር አርከበ እቁባይ ፣የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያ አህመድን ጨምሮ ብዙዎች በግል ተጠቃሚ መሆናቸው ተመልክቷል።
አቶ አርከበ እቁባይ ከባቡር ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ በብድር ከሚመጣው ገንዘብ ከፍተኛ ተጠቃሚ በመሆናቸው ከአዲስ አበባ ሀዋሳ የባቡር ሀዲድ ለመዘርጋት ያቀረቡት እቅድ ባበዳሪ መጥፋት ተግባራዊ እንዳልሆነም ታውቋል።
አዋጪ እንዳልሆነ የሚገልጹት ባለሙያዎችም የፍጥነት መንገድ ከተዘረጋ በኋላ ለሀዋሳ የባቡር መንገድ ለመዘርጋት የተያዘው እቅድ አቶ አርከበና በዙሪያቸው ያሉትን ከመጥቀም ውጭ ጥቅም እንደማይኖረው ይገልጻሉ።