ሰኔ ፳፯ ( ሃያ ሰባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሶማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር ሃሰን ዓሊ ከይሬ ለ29ኛው አፍሪካ ሕብረት ስብሰባ በመጡበት በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ታስረው ሲሰቃዩ የነበሩ 120 ሶማሊያዊያን እስረኞችን ሰኞ እለት አስለቁ።
ሚንስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ”ሁለታችንም መንግስታት በደረስንበት የጋራ ስምምነት አማካኝነት 120 ሶማሊያዊያን ዜጎቻችንን ከእስር ተፈተዋል።” በኢትዮጵያ እስር ቤት ውስጥ አሁንም ድረስ ስላሉት ሶማሊያዊያን እስረኞች ግን ያሉት ነገር የለም። በነጻ ከእስር የተፈቱት እስረኞች በቀጣይ ቀናት ውስጥ ከሚንስትሩ ጋር ወደ ሶማሊያ ይጓዛሉም ተብሎ ይጠበቃል።
ሶማሊያዊያኑ እስረኞች ከአስር ዓመታት በላይ በእስር የቆዩ ሲሆን ምንም ዓይነት ክስ ሳይቀርብባቸው በእስር ቤት ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው ቆይተዋል። በተለያዩ እስር ቤቶችች ውስጥ ሰብዓዊ መብታቸው ተገፎ ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው ከነበሩ ሶማሊያዊያን ታሳሪዎች ውስጥ በእስር ላይ እያሉ ሕይወታቸውን ያለፈም ይገኙበታል።
በኢትዮጵያ ሁለት አሃዝ ያለው እድገት እንዳለ በማስመሰል ጎብኝዎች እና ዲፕሎማቶች ቢገረሙም በአገሪቱ ያለው እውነተኛ ሁኔታ ግን ሁለት ዓይነት ገጽታዎች አሉት። በምጣኔ ሃብት ያደገች እና ፖለቲካዊ መረጋጋት የሰፈነባት አገር መስላ ብትታይም ይህ ሁሉ ግን ከታይታ የዘለለ አይደለም። አብዛሃኛው ኢትዮጵያዊ ዜጋ በመሳሪያ አፈና ስር የሚገኝና እያንዳንዱ ግለሰብ በፍርሃት ድባብ ውስጥ ይገኛል። ከ1991 እ.ኤ.አ. ጀምሮ መንበረ ስልጣኑን የያዘው ገዥው ፓርቲ ለብቻው ሁሉንም የፖለቲካ ምህዳር፣ የሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች እና የግለሰቦችን የግል ሕይወትም ጭምር ተቆጣጥሮታል።
በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ውስጥ ያለው የእስረኞች አያያዝ ኢሰብዓዊና በሕይወት ለመቆየት አስቸጋሪ መሆኑን በተደጋጋሚ ጊዜያት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይገልጻሉ። እስረኞች ሰቆቃ ቶርቸርን ጨምሮ የሰው ልጅ ሊችላቸው ከሚችለው በላይ ሰብዓዊ ክብራቸውን የጣሱ ድርጊቶች በእስር ቤቶች ይፈጸምባቸዋል ሲል ሆርስ ሚዲያ ዘግቧል።