በኢትዮጵያ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ በእስራት ተቀጡ

ኢሳት (መጋቢት 1 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ ተከሳሾች ከአራት አመት እስከ 21 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን የፌዴራሉ ፍርድ ቤት ሃሙስ አስታወቀ።

ማንነታቸውን ያልተገለጸው ተካሳሾች የአልቃይዳ አልሻባብ የምስራቅ አፍሪካ የሽብር መረብ ውስጥ አመራርና አባል በመሆን ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን የቀረበባቸው ክስ ማመልከቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

በሃገሪቱ ህግ ከፍተኛ ነው የተባለው ቅጣት የተላለፈባቸው 28ቱ ተከሳሾች ከ13 አመት በፊት ጀምሮ የሽብር ስልጠና ሲወስዱ መቆየታቸውንና በ1988 አም ወደ ጎረቤት ሶማሊያ በማቅናት የአልቃይዳ አልሻባብ ቡድንን እንደተቀላቀሉ ከሳሽ አቃቤ ህግ ለፍርድ ቤት አስረድቷል።

ከአምስት አመት በፊት ጀምሮም ተከሳሾቹ በሃገር ውስጥ በድብቅ በመንቀሳቀስ የተለያዩ የሽብር ድርጊቶችን በመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል ተብሏል።

በቁጥጥር የተያዙበት ስፍራና ጊዜ ያልተጠቀሰው ተከሳሾች የተመሰረተባቸውን የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ማስተባበል ሳይችሉ በመቅረታቸው ከአራት እስከ 21 አመት የሚደርሰው የእስር ቅጣት እንደተላለፈባቸው የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ገልጿል።