በኢትዮጵያ ኢንተርኔት እንዲዘጋ በመደረጉ የዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደደረሰ ተገለጸ

ኢሳት (ኅዳር 26 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ባለፉት 11 ወራቶች የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲዘጋ በመደረጉ በመንግስት ላይ የዘጠን ሚሊዮን ዶላር ወይም የ200 ሚሊዮን ብር አካባቢ ኪሳራ ማስመዝገቡን አንድ አለም አቀፍ ተቋም አስታወቀ።

መቀመጫውን በዚሁ በአሜሪካ ያደረገው ዘ-ብሩኪንግስ ኢንስቲቲዩቱ በሃገሪቱ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከሃምሌ 1 ፥ 2015 አም እስከ ሰኔ 30 2016 አም የኢንተርኔት አገልግሎት በተለያዩ ምክንያቶች ዝግ ተደርጎ መቆየቱን አውስቷል።

አገልግሎቱ ተዘግቶ በቆየበት ወቅት መንግስት የዘጠን ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ኪሳራ እንደደረሰበት የተቋሙ ምክትል ፕሬዚደንት ዳሬል ዌስት (Darrel West) ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

Bahirdar AIDS Resource Centre is always filled with youths usingየአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መደረግን ተከትሎ የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ ከሃምሌ ወር ጀምሮ የደረሰ ኪሳራ በዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ውስጥ አለመካተቱን ለመረዳት ተችሏል።

ባለፈው አመት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቆጣጠር ሲባል መንግስት የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲዘጋ አድርጎ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

ይህንኑ ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቆጣጠር በሚል አገልግሎቱ ይፋዊ በሆነ መንገድ ከጥቂት ወራቶች በፊት ዝግ የተደረገ ሲሆን፣ እርምጃው በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የአሜሪካና የተለያዩ ሃገራት ኤምባሲዎች እንዲሁም አለም ቀፍ ተቋማት መንግስት በወሰደው ዕርምጃ ምክንያት ስራቸውን ማከናወን እንዳልቻሉ ሲገልጹ ቆይተዋል።

በኢትዮጵያና በሌሎች 19 ሃገራት ላይ ጥናትን ያካሄደው ዘብሩኪንግስ ኢንስቲትዩት ባለፈው አመት ብቻ በእነዚሁ አገራት በኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ የ2.4 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ መድረሱን አመልክቷል።

የእለት ከእለት ስራቸው ከቴክኖሎጂው ጋር የተቆራኘ በርካታ ኩባንያዎች በአገልግሎቱ መቋረጥ ሳቢያ ኪሳራ እየደረሰባቸው እንደሆነ የድርጅቱ ሃላፊዎች አክለው ገልጸዋል።

በአዲስ አበባና የክልል ከተሞች የሚገኙ በርካታ ሆቴሎች እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉ በስራቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ሲገልጹ ቆይተዋል። የተባበሩት መንግስታት ተወካይ ተቋማትም የእርዳታ ስራን ጨሮ አለም አቀፍ ግንኙነታቸው ክፉኛ መጉዳቱን በመግለጽ ላይ ናቸው።