ሰኔ ፰ ( ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም /World Food Program/ በኢትዮጵያ በደረሰው ድርቅ ምክንያት ከሰኔ ወር መቋጫ ጀምሮ ለርሃብ ተጋላጭ የሆኑና አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ጭማሪ አሳይቷል። እንደ ድርጅቱ መግለጫ ከሆነ 7.8 ሚሊዮን የነበረው አፋጣኝ የእለት እረዴት ጠባቂዎች ቁጥር ወደ 8 ሚሊዮን ማሻቀቡን አስታውቋል። ይህም 8 ሚሊዮን በሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተግዳሮትን ደቅኗል።
የኢትዮጵያ የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ለአሾሼትድ ፕረስ የዜና ወኪል እንዳሉት ርሃብተኞችን ለመታደግ የአንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ያስፈልገናል ብለዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ላለፉት ሶስት ዓመታት ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመጣሉ አብዛሃኛው ዜጋ ለርሃብ አደጋ ተጋላጭ ሆኗል። ወንዞች፣ ምንጮች እና የውሃ ተፋሰሶች ደርቀዋል። የአየር ትንበያ ባለሙያዎች በኤሊኖ አየር መዛባት ምክንያት የተከሰተው ድርቅ አድማሱን ያሰፋል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል። ድርቁ የቤት እንስሳትን በመጉዳቱም በአርብቶ አደሮቹ እለታዊ እንቅስቃሴ ላይ እክል ፈጥሯል። ባለፉት አራት ወራት ብቻ የርሃብተኛ ዜጎች ቁጥር በሁለት ሚሊዮን ጭማሪ ማሳየቱን ድርጅቱ በሪፖርቱ አመልክቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ቀውስ ቡድን የእርዳታ ድርጅቶች በመርዳት በመዳከማቸው ምክንያት አፋጣኝ የሆነ እረድኤት በወቅቱ ለማግኘት አለመቻሉን አስታውቋል። አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ማግኘት ካልተቻለ አደገኛ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ሲል አሳስቧል። በተለይም ሕጻናት የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሾች ይሆናሉ ሲል አስጠንቅቋል።
በዓለም ሕጻናት እድን ድርጅት /Save the Children/ የኢትዮጵያ አስተባባሪ የሆኑት ጆን ግርሃም ስለሁኔታው አሳሳቢነት ሲገልጹ ”የምግብ አቅርቦቱ ተሟጦ ካለቀ በኋላ ምን እንደሚፈጠር የምናውቀው ነገር የለም። የርሃብ ተጠቂዎቹ በቂ የሆነ ምንም ዓይነት ምግብ አቅርቦት ስለማያገኙ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተለይ ለተመጣጠነ የምግብ እጥረት ተጋላጭ የሆኑ ሕጻናት ሕይወት በአስከፊ እና አደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኛል።” ሲሉ የርሃቡን መጠነሰፊ ሰቆቃ ለፈረንሳይ የዜና ወኪል AFP ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ የርሃቡን አስከፊነት አምነዋል። ድርቁ በቀጣይ ከሚመጣው የርሃብ አደጋ አስቀድሞ የመከላከል ስራዎች በተሻለ ሁኔታ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ፌስ አፍሪካ ዘግቧል።