በኢትዮጵያ አምስት ቢሊዮን ብር የሚፈጅ የኬሚካል ፋብሪካ ሊገነባ ነው

ኢሳት (መጋቢት 16 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ ነው የተባለና አምስት ቢሊዮን ብር የሚፈጅ የኬሚካል ግንባታ ለማካሄድ በትግራይ መልሶ ማቋቋምና በአንድ የቻይና ኩባንያ አርብ ስምምነት ተፈረመ።

በመቀሌ ከተማ አቅራቢያ ይገነባል የተባለውን ይህንኑ የፋብሪካ ስምምነት የትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅት ሃላፊ የሆኑት ወ/ሮ አዜብ መስፍንና የቻይናው CEO ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተወካይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ከ 250 ሚሊዮን ዶላር ይፈጃል የተባለውን ይህንኑ ፋብሪካ በመገንባቱ ሂደትም ሱር ኮንስትራክሽንና መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ የተሰኙ የትግራይ መልሶ ማቋቋም እህት ኩባንያዎች በንዑስ ተቋራጭነት እንደሚሳተፉም ታውቋል።

በቀጣዮቹ 18 ወራት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የኬሚካል ፋብሪካው በዋነኛነት በአመት 60ሺህ ቶን ፒቪሲ እና 50ሺህ ቶን ኮስቲክ ሶዳን ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል።

የተለያዩ ተጨማሪ ኬሚካሎችንም ያመርታል ተብሎ የሚጠበቀው ይኸው ፋብሪካ ከውጭ ሃገር የሚገቡ ምርቶቹን በማስቀረት የሃገር ውስጥ ገበያን ለመቆጣጠር እቅድ እንዳለውም ለመረዳት ተችሏል።

ሱር ኮንስትራክሽንና መስፍን እንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ በመንግስት የሚከናወኑ በርካታ ፕሮጄክቶችን በጨረታ በመረከብ የአባይ ግድብ ግንባታን ጨምሮ በመንገዶችና በሌሎች የግንባታን ዘርፎች ተሰማርተው እንደሚገኙ ይታወቃል።