በውጭ ምንዛሪ ቀውስ የሚታወሰው የህዉሃት/ኤህአዴግ አገዛዝ በ2009 አ.ም አመታዊ የውጭ ወለድ ክፍያው ከ3 ቢሊዮን ብር ወደ 10 ቢሊዮን ብር እንዲሁም አመታዊ የመንግስት የውጭ እዳ ክፍያ ከ14 ቢሊዮን ብር ወደ 25 ቢሊዮን ብር አድጓል። በዚህ ምክንያት ችግሩ የህዉሃት መራሹ መንግስት አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተው እንደሆነ ተገልጿል።
ከፊሉን የውጭ እዳ ለማቃለል ከወጭ ንግድ ከሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እሸፍናለሁ በማለት ቢገልጽም በየአመቱ ከውጭ ንግድ የሚገኘው ገቢ እየቀነሰ መሄዱ እቅዱን ለማሳካት ችግር እንደገጠመው ለማወቅ ተችሏል።
በ2008 አ.ም የውጭ ንግድ ገቢ 72 ቢሊዮን የነበረ ሲሆን እየተገባደደ ባለው 2009 አ.ም የወጭ ምርት ገቢው በ5 ቢሊዮን ብር ቅናሽ ማሳየቱን አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘግቧል። በተመሳሳይ ሁኔታ በ2008 አ.ም የነበረው የመንግስት የውጭ እዳ ከ540 ቢሊዮን ብር በአንድ አመት ውስጥ ብቻ 35 ቢሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት ወደ 575 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ህዉሃት መራሹ መንግስት በሚከተለው ከመጠን በላይ ያለፈ የብር ህትመት ምክንያት የብር ዋጋ እየወረደ በመሄዱ የሸቀጦች ዋጋ በየአመቱ ከ10 በመቶ በላይ እየናረ መሄዱን ከንግድ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች አመልክተዋል።