(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 10/2009)
የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ቴድሮስ አድሃኖም በኢትዮጵያ በጋዜጠኝነቱ የታሰረ የለም አሉ
በቅርቡ የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነው የተሾሙት ቴድሮስ አድሃኖም ኢትዮጵያ ውስጥ በጋዜጠኝነቱ ወይም ሀሳቡን በነጻነት በመግለጹ የታሰረ ጋዜጠኛ የለም ሲሉ ከፎረን አፌርስ መጽሔት ጋር ባደረጉት ምልልስ ተናግረዋል።
የማህበረሰብን ጤና የተመለከቱ መረጃዎችን ለሕዝብ ለማዳረስ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ቀደም ብሎ መናገራቸውን ተከትሎ እርሳቸው አባል የነበሩበት የኢትዮጵያ መንግስት በ2016 16 ጋዜጠኞችን ማሰሩንና ይህም በአለም ካሉ 5 የፕሬስ መብት ጭፍላቂ ሀገራት ተርታ እንዳሰለፋት የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ሲፒጄን በመጥቀስ ጋዜጠኛው ጥያቄውን አቅርቦላቸዋል። ይህ ቃለ መጠይቅ የአለም ጤና ድርጅትን የተመለከተ መሆን እንዳለበትና እሳቸው ከድርጅቱ ጋር ስላላቸው ግንኙነት እንጂ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ መጠየቅ እንደማይገባቸው ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አሁን ከሚሰሩት ስራ ጋር ጥያቄው ምንም ግንኙነት የለውም በማለት መልስ መስጠት ያለፈለጉት ቴድሮስ አድሃኖም ጋዜጠኛው ጥያቄውን ቀየር በማድረግ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያላቸው ቁርኝት አሁን የሚሰሩትን ስራ ያሳንስብዎታል ለሚሉ ወገኖች ምን መለስ አለዎት ሲል ጥያቄውን አቅርቦላቸዋል። እሳቸውም ቀደም ብለው ሸሽተውት ወደነበረው ጉዳይ በመግባት ኢትዮጵያ ውስጥ በነበርኩበት ግዜ ሀሳቡን በነጻነት በመግለጹ የታሰረ ጋዜጠኛ የለም።የታሰሩት ሕግን በመጣሳቸው ነው ሲሉ ተሳልቀዋል። ጋዜጠኞች በአሜሪካ ያሉትም ጭምር አንድን ሕግ ሊወዱትም ላይወዱትም ይችላሉ።ነገር ግን ሕጉን መጣስ አይችሉም ሲሉ የማይገናኝ ማነጻጸሪያ አቅርበዋል። መልሰው ደግሞ ሚዲያ የሕዝብ አይንና ጆሮ ነው መንግስትም ችግሩን ለማስተካከልና ስለ ስራው ግብረ መልስ ለማግኘት ይጠቀምበታል።እኔም ኢትዮጵያ በነበርኩበት ግዜም ይህን ነበር የምናደርገው ሲሉ በኩራት ተናግረዋል።
በተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በአለም ካሉ አምባገነን መንግስታት የጋዜጠኞችን መብት በመጣስ በማሰርና በማንገላታት በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ግንባር ቀደም መሆኑን በየአመቱ በሚያወጧቸው ሪፖርቶች እየጠቀሱ ባሉበት ሁኔታ ቴድሮስ አድሃኖም ይህን መግለጫ መስጠታቸው እንግዳ ባይሆንም ግርምትን ጭሯል።
በሌላ በኩልም በኢትዮጵያና በአካባቢዋ ባሉ ሀገራት የተከሰተውን ኮሌራ የኢትዮጵያ መንግስት እንደ አካባቢው ሀገራት የኮሌራ ወረርሽኝ ብሎ ለምን አላወጀም የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር። እሳቸውም ጥያቄውን በማጣጣል ኮሌራም አልነው ሌላ ስም ሰጠነው ዋናው የመከላከያ እርምጃ መውሰዳችን ነው ሲሉ መልስ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በማለት እየጠራ ባለው ነገር ግን በውጪ የጤና ባለሙያዎችና ድርጅቶች የኮሌራ ወረርሽ መሆኑ በተረጋገጠው በሽታ በተለይ በሶማሌ ክልል በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ማለቃቸው ተነግሯል።