በኢትዮጵያ በዲያስፖራው ከተያዙ 744 ፕሮጀክቶች ውስጥ ሩቡ እንኳን በአግባቡ ተግባራዊ አልሆኑም ተባለ፡፡

(ሰባት)ቀን ፳፻፮ /  ኢሳት ዜና :-ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ጀኔራል የተገኘ መረጃ  በግምት ከ2-3 ሚሊዮን የሚደርሱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የአለም ከፍሎች ቢኖሩም ለአገራቸው ያላቸው አስተዋጽኦ ግን አነስተኛ ነው ብሎአል።

አውሮፖና አሜሪካ የኢትዮጵያውያኑ ዳያስፖራዎች ዋነኛ መዳረሻዎች ሲሆኑ በርካታ የዳያስፖራው አባላትም በእነዚሁ አህጉራት ይገኛሉ ይላል።

እውቅና ያገኙ ተመራማሪዎች ፤ የጤና ባለሙያዎች ፤የዩንቨርስቲ መምህራን ፤በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሰሩ ባለሙያዎች ፤ድርጅቶችን በመክፈትና በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ኢንቨስትመንት ተቀጣሪዎችም መኖራቸውንም ሰነዱ ያወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት እንደ ህንድና ቻይና አገራት በአገራቸው ላይ ያላቸውን የልማት ተሳትፎ ለማጠናከር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ቢሆንም በተለይ ከሜሊኒየም መባቻ ጀምሮ የዳያስፖራው ተሳትፎ እየጨመረ መጥቷል ቢባልም በተግባር የሚታየው የዚህ ተቃራኒ ነው ብሎአል።

‹‹የዲያስፖራ ተሳትፎ ዓለም አቀፋዊና የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታዎች›› በሚል ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው

 በ2005 ዓ.ም በተወሰኑ ከተማ አስተዳደሮች በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በዲያስፖራው ስም ተመዝግበው ለመንቀሳቀስ ካመለከቱት 744 ኘሮጀክቶች መካከል በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት ወይም ምርት መስጠት የጀመሩት 120 ኘሮጀክቶች ብቻ ናቸው።

ሁሉም ፕሮጀክቶች ወደስራ ከገቡ ለአንድ ሚልየን 82,972 ለሚሆኑ ዜጐች ቋሚ የሥራ እድል እንዲሁም ለ2 ሚልየን 131 ሺ 200 ዜጐች ጊዜያዊ የሥራ እድል ይፈጥራሉ ብሎ መንግስት ተስፋ ማድረጉም ተመልክቷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ጀኔራል ዲያስፖራው በአገሩ ላይ የሚፈለገውን ሚና ለመጫወት ያልቻለባቸውን መንገዶች ዘርዝሮ አቅርቧል። በቅድሚያ የቀረበው ምክንያት  ዲያስፖራው በሀገሪቱ መንግስት ላይ ያለው አመለካከት የተዛባ መሆን የሚለው ይገኝበታል።

ዲያስፖራው በአሁኑ ስዓት ኢህአዴግን ከመደገፍ ይልቅ በኤርትራ ለሚንቀሳቀሱ የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ ቡድኖች መደገፍ ይፈልጋል የሚለው ሰነዱ፤ ከመንግስትም ወይም ከተቃዋሚዎች ከመጎዳኘት ይልቅ መሃል ሰፋሪ መሆን የሚመርጡ የዲያስፖራ አባላት መኖራቸውን ይገልጻል።

በክልሎች ያለው የመልካም አሰተዳደር ችግር ፤ሙስና ፤ ዲፕሎማቶች ተገቢውን ስራ አለማከናወናቸው በመንግስት በኩል የሚታዩ ድክመቶች ናቸው በማለት የሚጠቅሰው  ሰነዱ፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ በሚመጡ የዲያስፖራው አባላት የሚታዩ ችግሮች በማለት ከዘረዘሩዋቸው መካከል ደግሞ ”

በተሠጣቸው የኢንቨስትመንት ቦታ ላይ ለማልማት ያላቸው አቅም አናሳ መሆን፣ የተቀበሉትን ቦታ ለሌላ አካል ለማስተላለፍ መሞከር፤ ፈጥኖ ወደ ስራ አለመግባትና አጥሮ ማስቀመጥ፣  የመሬት ሀብት ስለሚባክን ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ቅሬታ መነሳት ፤እነሱ በሚፈልጉበት ጊዜና መንገድ ጉዳያቸው ካልተፈፀመ መንግስትን የማማረርና የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሆነ የማስመሰል ሁኔታዎች መኖር ፣

ከዳያስፖራዎቹ ከራሳቸው ምን እንደሚጠበቅና የኢንቨስትመንት አሠራር ህግን ያለማወቅ ፤ለጠየቁት ፕሮጀክቶች መሬት ማግኘታቸውን ሳያረጋግጡ ለፕሮጀክቶቻቸው አገልግሎት የሚውሉ ማሽነሪዎችን ግዥ ፈጽመው በወደብ የመጋዘን ኪራይ ያለአግባብ ወጭ እያወጣን ነው ብለው ማማረር ፤አብዛኛው ዳያስፖራ ወደ ክልሉ መጥቶ ለማልማት ሲፈልግ ቅድሚያ መረጃ የሚሰበስበው በየግለሰቡ መሆኑ” የሚሉት ይገኙበታል።

በአገር ውስጥ ያሉት የዳያስፖራ ተወካዮች ጉዳይ ለማስፈጸም ችግር ካጋጠማቸው ውጭ ለሚኖሩት ዳያስፖራዎች ችግሩን አጋኖ የመናገር ሁኔታ መኖር ፤በተወካዮቻቸው ድክመት ፕሮጀከቶቻቸው በሚፈልጉት መንገድ ካልተፈጸሙላቸው መንግስትን የማማረር ሁኔታ መኖር፣ በክልሉ  የተመዘገበውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ለውጥ አምኖ ለመቀበል ያላቸው ዝግጁነት አናሳ መሆን፤

ዳያስፖራው የኢንቨስትመንት ፈቃድ ካወጣ በኋላ ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር እንዲገባ ለማድረግ የሚሰጠው ድጋፍና የሚደረገው ክትትል  አናሳ መሆን ፤ዳያስፖራው ለሚያቀርበው ጥያቄ አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ በመረጃና በአሰራር ላይ ተመስርቶ በወቅቱ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ

ነገ ዛሬ በማለት ስለሚያጉላላና ለአላስፈላጊ ወጭ ስለሚዳረግ መንግስትን ከማማረራቸውም በላይ ሌሎች ዳያስፖራዎችን ወደ በሀገራችን መጥተው በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑ በሰነዱ ላይ ተዘርዝሮ ቀርቧል።

“ከፍተኛ አመራሮች ወደ ውጭ አገራት ሂደው ዳያስፖራውን ወደ ሀገሩ መጥቶ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች እንዲሳተፍና ሀገሩን እንዲደግፍ ሲያወያዩት ‘ኑና አልሙ ትላላችሁ ወደ ክልላችን ስንሄድ ግን እንጉላላለን፤ተገቢውን አገልግሎት አናገኝም፤ የተሻሉ ሰዎችም ተስፋ ቆርጠውና ክልላቸውን ጠልተው ሲመለሱ እናያለን…’ በማለት እንደሚናገሩ ሰነዱ ይገልጻል።

ሰነዱ በትግራይ 95፣ በአማራ 120፣ በአፋር 60፣ በቤንሻንጉል 51፣ በኦሮምያ 114፣ በሀረሪ 96፣ በሶማሊ 83፣  በደቡብ 111 እንዲሁም በጋምቤላ 33 የዲያስፖራ ፕሮጀክቶች መመዝገባቸውን ያሳያል። ከህዝብ ብዛት አንጻር ሲነጻጸር በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች የዲያስፖራው ተሳትፎ እጅግ አነስተኛ ነው። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚኖርባቸው በእነዚህ ክልሎች የመጣው ዲያስፖራ ተሳትፎ አነስተኛ መሆን ከፖለቲካው ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆን እና አለመሆኑ በሰነዱ ውስጥ አልተገለጸም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም የሚመሩት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከ120 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን አስከፊ በሆነ ሁኔታ እንዲባረሩ ቀሪዎቹም ተመሳሳይ እጣ እንዲገጥማቸው በማድረጉ በኩል ተጠያቂ መሆኑን አንዳንድ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ለኢሳት ገልጸዋል።

እነዚሁ ሰራተኞች እንደገለጹት የመንግስት የዲያስፖራ ፖሊሲ በአንቀጽ 5 ላይ ” ህጋዊ ወረቀት ለሌላቸው በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሚኒስቴሩ ህጋዊ የመታወቂያ ወረቀት  በመስጠት በችግራቸው ጊዜ ለመድረስና እና በአገሪቱ ልማት ተሳታፊ እንዲሆኑ ያበረታታል፣ ችግር ባጋጠማቸው ጊዜም አስፈላጊውን ክትትል፣ ድጋፍና እርዳታ ያደርጋል” የሚል ተደንግጎ ቢገኝም፣በሪያድ የሚገኘው ኢምባሲም ሆነ በጅዳ የሚገኘው ቆንስላ ለኢትዮጵያውያኑ ህጋዊ ወረቀት በመስጠት አሁን የተከሰተው አደጋ እንዳይከሰት ማድረግ ይችል ነበር፣

ለዚህም መንግስት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ነው ሲሉ እነዚሁ ሰራተኞች ገልጸዋል። ከዚህ የበለጠ የከፋ አደጋ አልነበረም የሚሉት ሰራተኞች፣ መስሪያ ቤቱ ያሳየው ተነሳሽነት እና በሁዋላም ከተጠያቂነት ለማምለጥ በሚል ከስደተኞች ጋር ፎቶ ግራፎችን በመነሳት ችግሩን ለማድበስበስ ተሞክሯል ይላሉ።

ህጉ የወጣው ለይስሙላ ነው ካልተባለ በስተቀር በዲያስፖራ ፖሊሲ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ለኢትዮጵያውያኑ ህጋዊ ወረቀት በጊዜው በመስጠት ችግሩን ማስቀረት ይቻል ነበር የሚሉት እነዚሁ ሰራተኞች በመካከለኛው ምስራቅ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ችግር ፈጥነው በመድረስ ያሳዩት ተሳትፎ በፖሊሲው ላይ ሳይቀር መገለጹን አውስተዋል።

በአንቀጽ አንድ ተራ ቁጥር 2 ላይ ” አብዛኞቹ ሙያ የሌላቸው ወይም በከፊል ሙያ ያላቸው በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መንግስትና አገር ጥሪ ባቀረበላቸው ጊዜ በፍጥነት የሚደርሱ፣ በአገራቸው የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚሳተፉና ለቤተሰቦቻቸው በየጊዜው ተቆራጭ ገንዘብ የሚልኩ ናቸው” ሲል ይገልጻቸዋል።

የአለም ባንክ ኢትዮጵያ በእየአመቱ በውጭ ከሚገኘው ኢትዮጵያዊ 3 ቢሊዮን 200 ሚሊየን ዶላር እንደምታገኝ የገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት በአረብ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ህጋዊ የመታወቂያ ወረቀት በማደል ችግሩ እንዳይከሰት ለማድረግ ለምን እንዳልቻለ እስካሁን አሳማኝ ማብራሪያ አልሰጠም።