መጋቢት ፳፩ (ሃያ አንድ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የበልግ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ አለመጣሉን ተከትሎ በተፈጠረ ከፍተኛ ድርቅ ምክንያት በምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸውን ወርልድ ቪዥን አስታውቋል።
የአየር ትንበያዎች በመጪዎቹ ወራቶች ካሁኑ በከፋ ሁኔታ የዝናብ እጥረቱ ተባባሶ እንደሚቀጥልና ከቀድሞው 45 በመቶ ከመቶ በታች የሆነ ዝናብ ሊዘንብ እንደሚችል ያመለክታሉ።
ከምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አርብቶ አደር አካባቢዎች በተጨማሪ ድርቁ በአማራ ክልል በዋግህምራ፣ በደቡብ ትግራይ፣ በኦሮምያ ክልል በአርሲ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ሃረርጌ በረሃብ ሊጠቁ እንደሚችል ድርጅቱ አስጠንቅቋል። ባለፈው ዓመት በኦጋዴን አካባቢ በምግብ እጥረት ተጠቂ የነበሩ እርዳታ ሲደረግላቸው የነበሩ ሕጻናት ቁጥራቸው ከ3 ሽህ 817 ወደ 5 ሺህ 996 ከፍ ብሎአል።
የበልግ ምርት አምራች የሆኑ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ለከፍተኛ የርሃብ አደጋ እና ውሃ እጥረት መጋለጣቸውን ተከትሎ በተለይ በምስራቅ እና ምእራብ ኦሮሚያ፣ ሰሜን ሶማሌ እና ደቡብ ክልል ውስጥ ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል ሲል ወርልድ ቪዥን ሪፖርቱን አጠቃሏል።
የረሃብ አደጋ ያንዣበባቸው የትግራይ እና የአማራ ክልሎች ገዢዎች በቅርቡ በኦሮምያ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች እርዳታ መላካቸውን አስታውቀዋል። እንዲሁም የኢህአዴግ መሪዎች በቅርቡ በተመሳሳይ በድርቅ ለተጎዱ የሶማሊ ላንድ ዜጎች የእርዳታ እህል ልከዋል።