ኅዳር ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በየዓመቱ እየባሰበት የመጣው የኢትዮጵያ የዋጋ አለመረጋጋት አሁንም ተባብሶ መቀጠሉን የማእከላዊ ስታስቲክ ጽፈት ቤትን ዋቢ በማድረግ የዓለም የምግብ ድርጅት በወርሃዊ የጥናት ሪፖርቱ አመላክቷል። ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ 5.6% የነበረው የምግብ ፍጆታ በሕዳር ወር ወደ 3.4% ከፍ በማለት ጭማሪ አሳይቷል። ይህም በአገሪቱ ውስጥ የዋጋ ንረት ማስከተሉን የደንበኞች የዋጋ አመላካች Consumer Price Index (CPI) መረጃ አውጥቷል። በጥናቱ መሰረትየምግብ ውጤቶች ያልሆኑት ሸቀጦች ላይ ደግሞ 8.3% የዋጋ ንረት አሳይተዋል።
የማእከላዊ ስታስቲክ መረጃ እንደሚያመለክተው ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የምግብ ዋጋ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ የእህልና ጥራጥሬ፣ የወተት ተዋጾዎች፣ ሥጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም አልኮል አልባ ምርቶች ከፍተኛውን ጭማሪ ካሳዩት ውስጥ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። በአገር አቀፍ ደረጃ የበቆሎ ምርት ካለፈው ወር 5% ቅናሽ ቢያሳይም ካለፉት አምስት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ግን በአማካኝ 10 % የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል። ካለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ጋር ሲነጻጸር ደግሞ 30% መጨመሩን ጥናቱ አረጋግጧል። በተመሳሳይም የነጭ ማሽላ ዋጋ16% የጨመረ ሲሆን ካለፈው ዓመት ጋር በአማካኝ ሲነጻፀር 22% የዋጋ ጭማሪ ታይቶበታል።
የጤፍ ዋጋ በመላው የኢትዮጵያ ከተሞች ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን አብዛሃኛው የድሃው ኅብረተሰብ ክፍል ፍጆታ የሆነው የበቆሎ ምርት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። በሶማሊያ እና አፋር ክልሎች ካለቀረጥ የሚገቡት የፓስታ፣ ሩዝ፣ የምግብ ዘይት እና የስንዴ ዱቄት አሁን ከነበሩበት ምንም ዓይነት ጫምሬ አላሳዩም። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ንረት ካለፈው ዓመት የምርት ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጫማሪ ማምጣቱን ተከትሎ የዋጋ ንረት መከሰቱን ጥናቱ አመልክቷል። በኦሮሚያ ክልል ያቤሎ፣ ነገሌ ጊኒር፣ ሻሸመኔ፣ ደደር እና ጭሮ ከፍተኛው የዋጋ ንረት ካለባቸው ውስጥ በቀዳሚነት ተጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ በመኸር የምርት ወቅት ላይ ይህን ያህል ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መፈጠሩ በዜጎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል ሲል ሪሊፍ ዌብ ዘግቧል።