በኢትዮጵያ ስለተከሰተው ድርቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ

ጥር ፳፪ (ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምስራቃዊ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አዲስ ድርቅ መከሰቱንና 5.6 ሚሊዮን ዜጎች አፋጣኝ እርዳታ ካላገኙ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስጠንቅቋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ቀውስ ባለስልጣን ስቴፈን ኦብሪን በቀጠናው በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ባደረጉት ጉብኝት ሁኔታውን ሲገልፁ ”እዚህ አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በሕይወት ለመቆየት ፈታኝ በሆነ ትንቅንቅ ውስጥ ናቸው። ይህ ርሃብ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትል አስቀድመን ርብርብ ማድረግ ግድ ይለናል” በማለት በአጽኖት አሳስበዋል።
ካለፈው ዓመት ጀምሮ በምስራቅ አፍሪካ በተከሰተው የኢሊኖ አየር መዛባት ምክንያት 10.2 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ለርሃብ አደጋ ተጋላጭ ሆነዋል። ድርቁን ተከትሎ በተከሰተ የውሃ እጥረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት በሞሞታቸው ምክንያት በአርብቶ አደር ዞኖች ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት መፈጠሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሪፖርቱ ገልጿል።
ከሶስት ሳምንታት በፊት ከመላ ቤተሰቧ ጋር ከ70 ኪሎ ሜትር በላይ በእግር ተጉዛ ወደ መጠለያ ጣቢያ የመጣችው ሳራ አሊሶ የተባለች የድርቅ ተጠቂ ተፈናቃይ ከሃምሳ በላይ ከብቶቻቸው እንዳለቁባት ተናግራለች።
”ለራሴ የምበላው ምንም የለኝም። የአርባ ቀናት ጨቅላ ሕጻን ልጄን ታቅፌ እዚህ መጥቻለሁ። ሁላችንም ተርበናል። ዝናቡ በቶሎ እንዲጀምር ፀሎት እያደረግን ነው።” በማለት ሳራ አሊሶ ያጋጠማትን የርሃብ ሰቆቃ ምስክርነት ሰጥታለች።
ዩኒሴፍ በበኩሉ በምስራቅ ኢትዮጵያ ካለው የርሃብ አደጋ በተጨማሪ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ሶማሊዊያን ዜጎች ድንበር እየጣሱ መፍለስ መጀመራቸውን ጥቅሷል። ይህን ተከትሎ በቀጠናው ተጨማሪ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይፈጥር ስጋት መኖሩን ሎሳንጀለስ ታይምስ አክሎ ዘግቧል።
በደቡብ ኦሞ ዞን የሚታየውን ከፍተኛ ድርቅ በተመለከተ ኢሳት ተደጋጋገሚ ዘገባዎችን ካቀረበ በሁዋላ፣ አገዛዙ ለማመን ተገዷል።
በኢቢሲ/ኢቲቪ ዜና ጥር 19፣ 2009 ዓም የቀረቡ የድርቁ ተጎጂዎች መካከል አንድ የሃመር ወረዳ የቤተሰብ ኃላፊ ሁኔታውን ሲገልጹ ‹‹ ግማሽ ኩንታል በቆሎ በ700 ብር እየገዛን ነው፡፡በዚህ ዋጋ ለቤተሰቤ ምግብ ለማቅረብ ሁለት ከብቶች ሸጨኣለሁ፡፡›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ይህንን አስከፊ የድርቅ አደጋ ተከትሎ በቆላማ ወረዳዎች ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉ ያስረዱ ምንጮች በሃመር ወረዳ ሁሉም የገጠር ት/ቤቶች ተዘግተው መኪና መንገድ በሚያቋርጣቸው አራት ከተማ ቀመስ ቀበሌዎች / ዲመካ፣ ቱርሚ፣ አርቦሬና ወይጦ/ ቢራሌ ›› ያሉት ብቻ እያስተማሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡