በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ላይ ለመወያየት ሰሞኑን ወደ ጀኔቫ አምርተው የነበሩ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ተወቀሱ

ሰኔ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ላይ ለመወያዬት ሰሞኑን ወደ ጀኔቫ  አምርተው የነበሩ የኢህአዴግ ባለስልጣናት፦“አካሄዳችሁ፤የፈራችሁትን የዓረብ ስፕሪንግ እዛው እቤታችሁ ድረስ ሰተት አድርጎ የሚያመጣ እንጂ፤መፍትሄ ሊሆናችሁ አይችልም” ተብለው ተወቀሱ።

ባለስልጣናቱ ይህ ወቀሳ የተሰነዘረባቸው፤ባለፈው ሐሙስ በስዊዘርላንድ-ጄኔቭ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ውስጥ፤ ሲቪኪዮስ -ለዜጎች ተሳትፎ ዓለማቀፋዊ ህብረት የተባለ ድርጅት-  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤን(ሰመጉ) ሪፖርት ለመስማት ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ  ነው።

በስብሰባው ላይ የጄኔቭ ነዋሪዎች፣ አምባሳደሮች  እና መቀመጫቸውን በተለያዩ አውሮፓ አገሮች ያደረጉ ድርጅቶች ተገኝተዋል።

የቀድሞው ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ( ኢሰመጉ) ፤ማለትም  የአሁኑ ሰመጉ ሪፖርት በሚያሰማበት ስብሰባ ላይ ለመካፈል ወደዚያው ያቀኑ ኢትዮጵያውያን ፕሮግራሙ እስኪጀመር ድረስ በነበራቸው የግል ጨዋታ ከመካከላቸው ፦”ኢሰመጉ አሁንም አለ ወይ? ጨርሶ ያጠፉት መስሎን ነበር እኮ” የሚል ጥያቄ መሰንዘሩ ተሰምቷል።

ሌላው ተሰብሳቢ ለተሰነዘረው ጥያቄ በሰጠው ምላሽ ፦”ኢሰመጉ አሁን ሰመጉ ነው የሚባለው።ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል እንዳይጠቀሙ ተከልክለዋል።ኢትዮጵያን እስካልጨመሩ ድረስ መኖር ይችላሉ” ብሏል።

የሰመጉ ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ሞላ ባቀረቡት ዝርዝር ሪፖርት፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች  በ አሳሳቢ ሁኔታ በሚፈጸምባት ኢትዮጵያ ውስጥ ድርጅታቸው በነፃ ተዘዋውሮ ለመስራት የተጋረጡበትን እንቅፋቶች አመልክተዋል።

በተለይ ከቅርብ ዓመታት በፊት የ እርዳታ ድርጅቶችን አስመልክቶ ኢትዮጵያ የተገበረችው አዋጅ፤በህገ-መንግስቱ የተቀመጡ  ህግጋትን በመደፍጠጥ በሥራቸው ላይ ማነቆ  መሆኑን አቶ እንዳልካቸው ተናግረዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናልን በመወከል በስብሰባው የተገኙት ሚስ ክሌር ቤትሰን በበኩላቸው፤ መንግስታዊ ያልሁኑ ድርጅቶችን በሚመለከት በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግስታት ካወጧቸው ህጎች ሁሉ  እጅግ የጠበቀውን ያወጀችው ኢትዮጵያ ናት ብለዋል።

“የውጪ ድርጅት በ ኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች አቤቱታ ማቅረብም ሆነ መዳኘት አይችልም።ኢትዮጵያ ውስጥ የምስጢር እስር ቤቶች አሉ።ጋዜጠኞች ይታሰራሉ። የሰብዓዊ መብት ረገጣ የተለመደ ሆኗል” ሲሉም አክለዋል-ሚስ ክሌር።

ኬንያዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሚስተር ማይና ኪይይ ደግሞ፦”አገራችሁ  የ አፍሪካ ኩራት ነበረች..” በማለት ነው አስተያዬት መስጠት የጀመሩት።

ሚስተር ማይና  በመቀጠልም፦”በምኒልክ አመራር የተመዘገበው የ አድዋ ድል ታሪክ፤ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ መኩሪያን ተምሳሌት ነው።አፍሪካዊ በመሆኔ ታሪካችሁን እጋራለሁ።በነፃነት መቆየታችሁ፤እኛም ቀና ብለን እንድንሄድ እና ለመብታችን እንድንታገል ለመንገዳችን ብርሀን ሆኖናል።ተስፋ ሰጥቶናል” ካሉ በሁዋላ ፤”ሆኖም ላለፉት ዓመታት ስለ ኢትዮጵያ የምንሰማው ግን ምንድነው?” በማለት በሀዘን ጠይቀዋል።

ስለ ኢትዮጵያ የሚባለውን ነገር በ አካል ወደዚያው አቅንተው ከሁሉም ወገኖች ጋር በመነጋገር ለማጣራት ፍላጎት ቢኖራቸውም፤ ያቀረቡት የቪዛ ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ከ ዓመት በላይ መቆጠሩን ሚስተር ማይና ጠቁመዋል።

መድረኩ ለውይይት ክፍት መሆኑን ተከትሎ የ ኢህአዴግ ተወካዮች በሰመጉ ሪፖርት ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል።

በተለይ ጋዜጠኞች በሰበብ አስባቡ እየታሰሩ ነው የሚለውን እንደማይቀበሉ የጠቀሱት የ ኢህአዴግ ተወካዮች፤ጋዜጠኞች ቢታሰሩም ወንጀል ስለሠሩ እንጂ ፤ለምን ጻፋችሁ ?ተብለው አይደለም ብለዋል።

በስብሰባው የተገኙ አንዲት ኢትዮጵያዊ ለኢህአዴግ ተወካዮች በሰጡት መልስ፦”ህዝብን ማፈን የትም አያደርስም።አካሄዳችሁ፤የፈራችሁትን የዓረብ ስፕሪንግ እዛው እቤታችሁ ድረስ ሰተት አድርጎ የሚያመጣ እንጂ፤መፍትሄ ሊሆናችሁ አይችልም።የታመቀ ነገር አንድ ቀን መፈንዳቱ አይቀርም ።ከናንተ የተለየ ሀሳብ ወይም አመለካከት ያለውን ሰው በጠላትነት መፈረጁን ብትተውት ይሻላል”ሲሉ አሣስበዋቸዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide