በኢትዮጵያ መከፈት የነበረበት መደበኛ ትምህርት እንዲራዘም ተደረገ

ኢሳት (መስከረም 4 ፥ 2008)

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ዕልባት አለማግኘቱን ተከትሎ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በተያዘው ሳምንት መጀመር የነበረበት የ2009 ዓም የትምህርት ፕሮግራም እንዲራዘም ተደረገ።

የትምህርት ሂደቱ በተያዘው ሳምንት ሰኞ መጀመር የነበረበት ቢሆንም የትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶች ከመስቀል በዓል አከባበር በኋላ እንዲከፍቱ ምክክር በማድረግ ላይ መሆኑን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ተማሪዎች በበኩላቸው ትምህርት መቼ እንደሚጀምር ለማወቅ ወደ የትምህርት ቤታቸው ቢያቀኑም በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ የሚሰጣቸው አካል አለመኖሩን አስረድተዋል።

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ለወራት ሲካሄድ የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ በትምህርት ማስተማር ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ያሳደረ ሲሆን ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ በተያዘው አዲስ አመት ወደ ተለያዩ ኮሌጆች የሚገቡ ተማሪዎችም የትምሀርት መራዘም ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ታውቋል።

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በመካሄድ ላይ ያለውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ አካባቢዎች አሁንም ድረስ ትራንስፖርትን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራቸው ተስተጓጉሎ መገኘቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የትምህርት ሚኒስቴር ባለስልጣናት ወደተለያዩ የክልል ከተሞች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚመደቡ አዳዲስ ተማሪዎች ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል በማለት በጉዳዩ ዙሪያ እየመከረ መሆኑንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ለኢሳት ገልጸዋል።

በተያዘው አዲስ አመት የትምህርት ዘመን ወደ 100ሺ የሚጠጉ አዳዲስ ተማሪዎች ወደ ተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በትምህርት ማስተማር ሂደቱ ላይ ተፅዕኖን ያሳድራል ተብሎ ተሰግቷል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ ወላጆችና ተማሪዎች ትምህርት የሚጀምሩበት ወቅት በመገኛኛ ብዙሃን በኩል እንዲከታተሉ ለተማሪዎችና ወላጆች በመግለጽ ላይ መሆኑ ታውቋል።

ባለፈው አመት የትምህርት ዘመን በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የዩኒቨርስቲና የመደበኛ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በክልሉ እየፈጸሙ ነው ያሉትን ግድያና የጅምላ እስራት በመቃወም ተቃውሞን ሲያካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል።

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተማሪዎቹን ተቃውሞ ለመቆጣጠር በወሰዱት እርምጃ በርካታ ተማሪዎች የተገደሉ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ በእስር ላይ የሚገኙ ተማሪዎች  መኖራቸው የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

በተለያዩ አካባቢዎች ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ዕልባት ባለማግኘቱ ምክንያት የየክልል ባለስልጣናት ከነዋሪዎቹ ጋር በመምከር ላይ እንደሚገኙ ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ይኸው ለወራት የዘለቀው ተቃውም በመንግስት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስርዓት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የትምህርት ሚኒስቴር በሃገሪቱ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ መምህራንና የአስተዳደደር ሰራተኞች በአዲሱ የትምህርት ዘመን በሚኖረው የትምህርት አሰጣጥ ዙሪያ ሃገር አቀፍ ውይይት እንደሚያካሄዱ ማክሰኞ አስታወቀ።

የዩኒቨርስቲው አካላት የሚያካሄዱትን ውይይት ተከትሎ የወላጆችና የተማሪዎች መድረክ በቀጣዩ እንደሚካሄድ ሚኒስትሩ ለሃገር ውስጥ መገኛኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የወላጆችና የተማሪዎች የውይይት መድረክ እንደ ተጠናቀቀ ተማሪዎች ከመስከረም 18 ጀምሮ ትምህርት እንደሚጀምሩ አክለው ተናግረዋል።

ከ 20 በላይ በሚሆኑ ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመጀመር እየተጠባበቁ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።