ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2008)
ከተያዘው ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ ለምግብ ድጋፍ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር 18 ሚሊዮን መድረሱን የብሄራዊ አደጋ መከላከያ ኮሚቴ ማክሰኞ ይፋ አደረገ።
በአሁኑ ወቅት በድርቁ ምክንያት አስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ ከተጋለጡት 10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በተጨማሪ፣ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በምግብ ራስ ማስቻል ፕሮግራም ድጋፍን እንደሚሹ ኮሚቴው ገልጿል።
በተያዘው አመት በአገሪቱ የተከሰተው የድርቅ አደጋ ባይከሰትም ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉት ሰዎች የምግብ ዕርዳታን የሚፈልጉ እንደሆነ የኮሚቴው ሃላፊ የሆኑት ኮሚሽነት ምትኩ ካሳ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ይሁንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተረጂዎች ዕርዳታ እየቀረበላቸው እንዳልሆነ በመግለጽ ላይ ሲሆን መንግስት በበኩሉ ለሶስት ወር የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ክምችት መኖሩን ማክሰኞ አስታውቀዋል።
በስድስት ክልሎች ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ለረሃብ የተጋለጡ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከልም ግማሽ ሚሊዮን ያህሉ በከፍተኛ የምግብ እጥረት የአካልና የጤና እክል እንዳጋጠማቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።
የበጋ ወቅቱ እየተጠናከረ በመሄዱም የተረጂዎች ቁጥር ሲያሻቅብ እንደሚችልና የህጻናቱ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ድርጅቱ አክሎ አመልክቷል።
የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የለጋሽ ሃገራት ምላሽ የሚፈለገውን ያህል አይደለም ሲሉ ማክሰኞ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጻቸውን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።