ኢሳት ዜና (መስከረም 12 ፣ 2008)
ኢትዮጵያን ጨምሮ በድሃ ሃገራት ከሚኖሩ ህዝቦች መካከል 90% የሚሆኑት የኢንተርኔት ተጠቃሚ አለመሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
ከአፍሪካ ዝቅተኛ የኢንተርኔት ሽፋን ያላት ኢትዮጵያም በአለም በአገልግሎቱ አሳሳቢ ተብለው ከተፈረጁ አስር አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ድርጅቱ በአመታዊ ረፖርቱ ገልጿል።
ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ቡሩንዲ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ረፐብሊክ፣ ጊኒ፣ ላይቤሪያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክና፣ ኒጀር በአለም በጣም ዝቅተኛ የኢንተርኔት ሽፋን ያላቸው አገራት ሲሆኑ፣ ከሁለት በመቶ በታች የሆኑ የየሃገሪቱ ዜጎች ብቻ አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ታውቋል።
በአለማችን ይኖራሉ ተብለው ከሚገመቱ ሰባት ቢሊዮን ህዝቦች መካከልም 57 በመቶ የሚሆኑት ለማህበራዊና ለኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያደርገውን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።
አመታዊ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንተርኔት አገልግሎት በሚስፋፋበት ሁኔታ ላይ ልዩ ምክክርን ያካሄዳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዝቅተኛ በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የሚደረግ የስለላ ተግባርና ቁጥጥርም ልዩ ትኩርት እንዲሰጠው ተገልጿል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ዝቅተኛ የኒንተርኔት አገልግሎት ከተመዘገበባቸው ሃገራት የኢንተርኔት ቁጥጥርም አሳሳቢ ችግር ሆኖ መገነቱን ከቀረበው ረፖርት ለመረዳት ተችሏል።
ደቡብ ኮሪያ፣ ኳታርና ሳውዲ አረቢያ፣ ለዜጎቻቸው አገልግሎቱን በስፋት ካዋሉ ሃገራት መካክል ግንባር ቀደም ሃገራት ሆነዋል።
ከ15 ኣመት በኋላ አገልግሎቱን በእጥፍ ለማሳደግ አለም አቀፍ ዘመቻ እንደሚካሄድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አክሎ አስታውቋል።