ኢሳት (የካቲት 15 ፥ 2009)
የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ድርጅቶች በኢትዮጵያና ጎረቤት ሶማሊያ በድርቅ ምክንያት ህይወታቸው አደጋ ላይ የተጋለጠ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ አፋጣኝ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪን አቀረቡ።
መቀመጫቸውን በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከተማ ያደረጉ የድርጅቱ የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪዎች በሁለቱ ሃገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሞት እና የጤና አደጋ ውስጥ መሆናቸውን እንደገለጹ ሮይተርስ ዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል በመባባስ ላይ ያለው አዲስ የድርቅ አደጋ የበርካታ ሰዎችን እና የቤት እንስሳትን ህይወት አደጋ ውስጥ እንደከተተው ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በዚሁ የድርቅ አደጋ ዙሪያ መግለጫን ያወጡ አለም አቀፍ የተባበሩት መንግስታት ተቋማት የአለም አቀፍ ማህበረሰብ አፋጣኝ ርብርብ የማያደርግ ከሆነ በአካባቢው የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ምክንያት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአስቸኳይ የድጋፍ በጀቱ 18.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲሰጥ መወሰኑን ገልጿል።
በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና የደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ተከስቶ ባለው በዚሁ የድርቅ አደጋ 5.6 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ተጋልጠው እንደሚገኙ ከወራት በፊት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ተወካይ የሆኑት ጄንስ ሌርክ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ እጅጉኑ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አስታወቀዋል።
ድርጅቱ ከአስቸኳይ የመጠባበቂያ በጀት የሰጠው የገንዘብ ድጋፍም፣ በሶማሌ ክልል ለከፋ የምግብ እጥረት በተጋለጡ 785 ሺ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ እንደሚውል አክለው ገልጸዋል። ባለፉት ጥቂት ወራቶች በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት በዚሁ የሶማሌ ክልል ብቻ የሞቱ ሲሆን፣ ድርቁን ለመከላከል በቀጣዮቹ ሁለት እና ሶስት ወራቶች ከፍተኛ ርብርብ ካልተደረገ በስፍራው የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአራት ክልሎች ተከስቶ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል በአጠቃላይ 948 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ይገልጻል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የአለም አቀፍ ማህብረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ በመጠየቅ ድርቁ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዲያስከትል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።