በኢሳና አፋር ብሔረሰቦች መካከል በተነሳ ግጭት 18 ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 17/2011) በኢሳና አፋር ብሔረሰቦች መካከል በተነሳ ግጭት 18 ሰዎች መገደላቸው ተገደሉ።

ባለፉት ሁለት ቀናት በሁለቱ ወገኖች ተካሄደ በተባለውና በመሳሪያ በታገዘው  ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ የገዋኔና አዋሽ አካባቢ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ፋይል

የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር አርዱፍ የኢትዮጵያ መንግስት የአፋር ንጹሃንን ህይወት እንዲታደግ በሚል መግለጫ አውጥቷል።

አርዱፍ በግጭቱ ከኢሳዎች ጀርባ የጅቡቲ መንግስት የመሳሪያ ድጋፍ ያደርጋል ሲል ከሷል። ግጭቱ ዛሬም መቀጠሉን ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።

በአፋርና ኢሳ መካከል ግጭት ሲከሰት የሰሞኑ የመጀመሪያው አይደለም።

ከቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘመን አንስቶ በሁለቱ ወገኖች መካከል ከቀላል እስከ ከባድ ጥፋት ያስከተሉ ግጭቶች ሲከሰቱ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

የሰሞኑ ግን የተለየ ነው ይለናል የአፋር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካድር ኢብራሂም።

የሰሞኑ ግጭት ከሁለቱ ወገኖች ይልቅ ከግጭቱ ፖለቲካዊ ትርፍ አስልተው የገቡ ሌሎች ሃይሎች አሉ ባይ ነው።

የሰሞኑ ግጭት መነሻ በኢትዮጵያ ከተከሰተው ለውጥ ጋር በተያያዘ ለውጡን የማይፈልጉ ሃይሎች የፈጠሩት ህብረት እንደሆነም ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ለማረጋገጥ ተችሏል።

በአፋር ክልል ዕንድፎ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የአፋር ክልልን ሰንደቅ ዓላማ በማውረድ የሶማሌን ክልልን በመተካት መነሻነት የተጀመረው ፍጥጫ ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት መቀየሩን የሚገልጹ ምንጮች በሁለቱም ወገኖች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ጠቅሰዋል።

በሁለት ቀናቱ ግጭት የ18 ሰዎች ህይወት ማለፉ ነው የተገለጸው።

መከላከያ ሰራዊቱ ባልደረሰባቸው አካባቢዎች አሁንም ግጭቱ መቀጠሉን አካድር ኢብራሂም ይገልጻል።

በገዋኔ፣ አዋሽና በአጎራባች አካባቢዎች በተፈጠረው በዚሁ ግጭት የተነሳ ወደ ትግራይና አዲስ አበባ የሚወስዱ መንገዶች መዘጋታቸው የተገለጸ ሲሆን ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ተሽከርካሪዎች መመላለስ እንዳልቻሉ ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር አርዱፍ የሰሞኑን ግጭት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የጅቡቲን መንግስት ከሷል።

በመሳሪያና ፖለቲካዊ ድጋፍ ከኢሳ ጎሳዎች ጎን ያለው የጅቡቲ መንግስት ነው ሲል የከሰሰው አርዱፍ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን እንዲታደግ ጥሪ አድርጓል።

አርዱፍ ከጅቡቲ በተጨማሪ የህወሃት ቡድን የግጭቱ ተዋናይ እንደሆነም ገልጿል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መንግስት ሰላም ለመንሳት በህወሃት በኩል የተሸረበ ሴራ አካል ነው ብሏል አርዱፍ።

ጉዳዩን በተመለከተ ከሶማሌ ክልል መንግስት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።