(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 11/2010)
በኢራቅ በአይሲስ ተይዛ የነበረችውን ሞሱል ለማስለቀቅ በተደረገ ፍልሚያ እስከ 11 ሺ የሚደርሱ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን የአሶሼትድ ፕሬስ የምርመራ ሪፖርት ይፋ አደረገ።
ይህ አሃዝ ከዚህ በፊት ሲነገር ከነበረው በ10 እጥፍ እንደሚልቅም ታውቋል።
በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ጦር በኢራቅ ወታደራዊ ሃይል በአይሲስ ተይዛ የነበረችውን ሞሱልን ለማስለቀቅ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተደረገ ጥቃት ከ9ሺ እስከ 11ሺ ንጹሃን ሰዎች ማለቃቸውን የአሶሼትድ ፕሬስ የምርመራ ዘገባ አጋልጧል።
ይህ በአሶሼትድ ፕሬስ የወጣው አሃዝ በጥምር ጦሩ ሃይልም ሆነ በኢራቅ መንግስት ወይም በአይሲስም ማረጋገጫ አልተሰጠውም።
በጥምር ጦሩ በተደረገ የአየርና የከባድ መሳሪያ ድብደባ ካለፈው አመት ጥቅምት እስከ ሐምሌ ድረስ 3 ሺ 200 ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን የምርመራ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
የዜና አገልግሎቱ መረጃውን መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከሬሳ ማቆያ ጣቢያዎች መሰብሰቡን ጠቁሟል።
የጥምር ጦሩ ግን 326 ለሚሆኑ ሰላማዊ ሰዎች ግድያ ብቻ ሃላፊነት እንደሚወስድ አስታውቋል።
የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ግን ጥምር ጦሩ ግድያውን ለማጣራት ወደ ሞሱል የላከው መርማሪ ቡድን እንደሌለ አስታውቋል።
አንድ ገለልተኛ የሆነና በኢራቅና በሶሪያ የተደረጉ የአየርና የከባድ መሳሪያ ድብደባዎችን መረጃ የሚሰበስብ ድርጅት ሃላፊ እንዳሉት ሞሱልን ለማስለቀቅ የተደረገው ጥቃት ባለፉት ሁለት ትውልዶች በአንድ ከተማ ከተደረጉ ጥቃቶች ሁሉ ትልቁ ጥቃት ነው ብለውታል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል ሲሉም አክለዋል ሃላፊው ክሪስ ውድስ።
ሃላፊው ሲቀጥሉም አይሲስ ለግድያው ትልቅ ሚና ቢጫወትም ንጹሃን ዜጎች እንዴት እንዳለቁ መመርመርና መረዳት ወደፊት በእንዲህ አይነት በከተማ በሚደረጉ ጦርነቶች ወቅት ብዙ ሕይወት እንዳይቀጠፍ ይረዳል ብለዋል።
አሶሼትድ ፕሬስ 9 ሺ 606 የሚሆኑ የሟች ስም ዝርዝሮችን በሞሱል ከሚገኝ የሬሳ ማቆያ ማግኘቱን ጨምሮ አስታውቋል።
በመቶ የሚቆጠሩ ሟቾች አሁንም ፍርስራሽ ውስጥ ተቀብረው ይገኛሉ።