(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 22/2011)በኢሕአፓ ስም በአዲስ አበባ አቀባበል የተደረገላቸው ሰዎች ድርጅቱን የሚወክሉ አይደሉም፥አባላችን አለመሆናቸውም ይታወቅልን ሲል ህጋዊ ነኝ ያለው ፓርቲ ያወጣው መግለጫ አመለከተ።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)’’አንድና አንድ ብቻ ነው”በሚል የወጣው የድርጅቱ መግለጫ እንዳመለከተው በአቶ መርሻ ዮሴፍ ስም አዲስ አበባ የገባው ቡድን እራሱን በአንጃነት የፈረጀ ነው።
እናም አርማውም፥ስሙም በሕግ የተመዘገበ ኢሕአፓ የተባለ ፓርቲ እያለ፥ አባላት ያልሆኑ ሰዎችን የድርጅቱ አመራሮች ናቸው በሚል በአዲስ አበባ አቀባባል መደረጉ ትክክል አይደለም ሲል መግለጫው አመልክቷል።
በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ምክንያት በማድረግ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች በመንግስት በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ወደ ሀገራቸው መግባታቸው ይታወሳል።
ከነዚህም መካከል የኢህአፓ አመራሮች ነን ያሉ የልኡካን ቡድን አባላት በመንግስት ባለስልጣናት በኩል በአዲስ አበባ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር።
ይህም ሆኖ ግን እነዚህን ቡድኖች ‘’የኢሕአፓ አባላት አይደሉም” በሚል መግለጫ ያወጡት አካላት ሕጋዊዎቹ ኢሕአፓዎች እኛ ነን ብለዋል።
ኢሕአፓ ካለፉት 40 አመታት በፊት የተቋቋመና ደርግንም ሆነ ኢህአዴግን በይፋና በሕቡ ሲታገል የቆየ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።