(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 22/2010)በኢሉባቡር መቱ ከሳምንት በፊት በተነሳ ግጭት ለተፈናቀሉና በመጠለያ ጣቢያ ለሚኖሩ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ በተቋቋመ ኮሚቴ አማካኝነት የተሰበሰበ የእርዳታ ገንዘብ ከደህንነት መስሪያ ቤት በወጣ ቀጥተኛ ትዕዛዝ መታገዱ ተሰማ።
ከ1500 በላይ ለሚሆኑት ለነዚህ ተፈናቃዮች የተሰበሰበው ገንዘብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4 ኪሎ ቅርንጫፍ በተከፈተ ሒሳብ ቁጥር የተቀመጠ መሆኑም ታውቋል።
በ4 ቀን ውስጥም ከ100 ሺ ብር በላይ መሰብሰቡንም የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
ኮሚቴዎቹ ገንዘቡ የታገደበትን ምክንያት ለማጣራት ወደ ባንኩ ቢሄዱም ያገኙት ምላሽ እረፍት ላይ የነበሩት የባንኩ ስራ አስኪያጅ ለዚሁ ጉዳይ ወደ ስራ እንዲገቡ ከደህንነት መስሪያ ቤት የተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑንና ስራ አስኪያጁም በሁኔታው መደናገጣቸውን ተናግረዋል።
ጉዳዩ ይመለከተዋል ወደተባለው ጠቅላይ አቃቢ ህግ የተጓዙት የኮሚቴው አባላት ባለስልጣናቱ የሉም የሚል ምላሽ ማግኘታቸውንም ለኢሳት ተናግረዋል።
ወደሚመለከተው አካል ሁሉ እንሄዳለን የሚሉት የኮሚቴው አባላት ገንዘቡን የሰበሰብነው ስርአቱ እንዲገለገልበት ሳይሆን የተጎዱ ወገኖቻችንን ለመርዳት ነው።
ስለሆነም ገንዘቡ ተለቆ ለተጎጂዎች እስኪደርስ ድርስ እስከመጨረሻው እንታገላለን ብለዋል።
ትላንት ባቀረብነው ዘገባ በኢሉባቡር ዞን በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመታደግ አለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ግሎባል አሊያንስ የላከው 25ሺ የአሜሪካን ዶላር ወይም 700 ሺ የኢትዮጵያ ብር ለተጎጂዎቹ እንዳይደርስ መደረጉ ይታወሳል።