በኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ውስጥ ፍርሃት ነግሷል

ኀዳር ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ በነሃሴ ወር ባካሄደው 10ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን ለመፍታት ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ እርምጃ እንደሚወድድ ውሳኔ ቢያሳልፍም አብዛኛው አመራር የችግሩ ሰለባ በመሆኑ በግንባሩ እርስበእርስ ከፍተኛ መፈራራትና መጠባበቅ መከሰቱ ታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት በሚለው ጉዳይ ላይ ልዩነት ያላቸው ሁለት ቡድኖች በግልጽ መውጣታቸው ታውቆአል፡፡ራሱን ንጹህ አደርጎ የሚያየው ቡድን ድርጅቱ አጥፊዎችን ጠራርጎ በማባረርና በማሰር ቁርጠኛ እርምጃ እንዲወስድ፣ የመንግስት ሚዲያዎች ጭምር በማጋለጥ ስራ ውስጥ እንዲሳተፉ ሌት ተቀን የሚጎተጉት ሲሆን ተቃራኒው ቡድን ደግሞ ችግሩ ቀለል ተደርጎ እንዲታይና ሁሉንም ነገር ሰዶ በማሳደድ መፍታት እንደማይቻል፣ ችግሩንም በቆየው ድርጅታዊ ባህል መሰረት በውስጥ ገምግሞ መፍታት እንደሚቻል በመናገር የተለሳለሰ አቋም እንዲያዝ የሚወተውት ሆኗል፡፡
የመጀመሪያው ቡድን በአብዛኛው ከትግሉ በሃላ ድርጅቱን የተቀላቀሉ አዳዲስ አመራሮችን ያቀፈ ሲሆን በዚህ ቡድን ውስጥ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ተካተውበታል፡፡ ሁለተኛው ቡድን በአብዛኛው ዋና ዋና የሚባሉ ታጋዮችን የያዘና በብዛት የህወሃት ነባር ታጋዮች የተካተቱበት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ቡድኖች የመልካም አስተዳደር ችግርን በመፍታት ጉዳይ ላይ የተስማሙ ቢመስሉም በአፈታቱና በእርምጃ አወሳሰድ ጉዳይ ላይ ስምምነት ስለሌላቸው የአንዳቸው አሸንፎ መውጣት የግድ የሚልበት ደረጃ መደረሱን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡
ከኢህአዴግ ጉባዔ በሁሃላ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከኢህአዴግ የድብቅነት ባህርይ ባፈነገጠ መልክ ከፍተኛ አመራሮች በኔትወርክ የተሳሰረ ህገወጥ መስመሮችን መዘርጋታቸውን ፍንጭ መስጠታቸውም ጉዳዩ ከባድ ደረጃ መድረሱን ያሳያል ብለዋል፡፡
ሟች ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የመልካም አስተዳደር ችግርና የሙስናና ብልሹ አሰራር መንሰራፋት አስጊ ደረጃ መድረሱን በመጥቀስ «አንድ እጃችንን ተይዘን ነው እየታገልን ያለነው… ወይ ልማታዊነት ወይንም ኪራይ ሰብሳቢነት ያሸንፋል» ብለው በመዛት በአደባባይ ችግሩን ለመፍታት አቅም እንዳነሳቸው መጠቆማቸውን ያስታሰው ምንጫችን፣ በአሁኑ ሰዓትም የአቶ ሃይለማርያም አመራር ተጨባጭ ሁኔታ ከዚህ ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ የመልካም አስተዳዳር ችግርን፣ የሙስናና ብልሹ አሰራርን ለማስተካከል የሚያደርገው ሙከራ የእርስ በርስ መበላላትን ሊያስከትል የሚችልበት አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱንም ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ሰኣት በሚኒስትር ደረጃ የተቀመጡ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ወታደራዊ መኮንኖች ከገቢያቸው በላይ ከፍተኛ ሃብት በማፍራት የሚታወቁ፣ በቤተሰቦቻቸው ስም ኢንቨስትመንት ውስጥ የገቡ፣ አንዳንዶቹም የግላቸውን መኖሪያ ቤት በከፍተኛ ዶላር ለውጭ ዜጎች በማከራየት በመንግስት ቤት የሚኖሩ ነጋዴ ባለለስልጣናት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ባለስልጣናት መልሰው የመልካም አስተዳደር ችግርና የሙስናና ብልሹ አሰራር ታጋዮች ሆነው መቅረባቸው ለብዙዎች አስቂኝ ቲያትር ሆኖባቸዋል።