በአፍሪካ አህጉር አክራሪነት እንዲስፋፋ ምክንያት የሆነው የየሀገራቱ መንግስታት ጭቆና ነው ተባለ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 17/2010)በአፍሪካ አህጉር አክራሪነት እንዲስፋፋ ምክንያት የሆነው የየሀገራቱ መንግስታት ጭቆና መሆኑን አንድ ጥናት ይፋ አደረገ።

ባለፉት 6 ወራት ብቻ አክራሪ ሃይሎቹ በአፍሪካ ምድር በወሰዱት ርምጃ 33 ሺህ ሰዎች ሲያልቁ በሚሊየን የሚቆጠሩ ደግሞ መፈናቀላቸው ተመልክቷል።

የተባበሩት መንግስታት የጥናት ቡድን በአክራሪ ሃይሎቹ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 500 ያህል ጽንፈኛ ግለሰቦችን ጭምር በማነጋገር ባደረገው ጥናት የመንግስታት የጭቆናና አፈና ድርጊት ግለሰቦች አክራሪ ቡድኖችን እንዲቀላቀሉ ምክንያት ሆኗል።

ቀደም ሲል በነዚህ ጽንፈኛ ቡድኖች ውስጥ ሲሳተፉ ከነበሩት 500ዎቹ ውስጥ 71 በመቶው አክራሪ ቡድኖችን ለመቀላቀል ምክንያት የሆናቸው የመንግስታት ጭቆና እንደሆነ ተናግረዋል።

በቤተሰባቸውና በጓደኞቻቸው ላይ ግድያን የጨመረ ድርጊት በመፈጸሙ በምሬትና በእልህ አክራሪዎቹን ማለትም ቦኮሃራምን የመሳሰሉ ቡድኖችን ለመቀላቀል ምክንያት ሆኖናል ሲሉ ይገልጻሉ።

ዘጋርዲያን የተባበሩት መንግስታትን የጥናት ውጤት መሰረት አድርጎ እንደዘገበው 83 በመቶ የሚሆኑት መንግስት ለጥቂቶች እንጂ ለብዙሃን አልቆመም የሚል እምነት እንዳደረባቸው ሲገልጹ 75 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እምነት እንደሌላቸውና የሕዝብ ናቸው ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።