በአፋር የተጀመረው ግጭት ቀጥሎ 8 ሰዎች ተገደሉ

ግንቦት ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በዛሬው እለት የኢሳ ተወላጅ የሆኑ ልዩ  ሀይል የሚባሉት ታጣቂዎች 8 የአፋር ከብት አርቢዎችን  ገድለዋል። የአካባቢው ህዝብም በስጋትላይ መሆኑ ታውቋል ። የአፋር ህዝብ መሬቱ ለሸንኮራ አገዳ ተክል ይወሰደብኛል ብሎ እየሰጋ ባለበት ጊዜ  ጥቃት መፈጸሙ ችግራቸውን ይበልጥ እንዳወሳሰበባቸው ተወላጆች ይናገራሉ።፣

አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የአካባቢው ተወላጅ እንደተናገሩት በዛሬው እለት በ7 ላንድ ክሩዘር መኪና የመጡ የኢሳ ልዩ ሀይል አባላት ከብቶችን ይጠብቁ ከነበሩ 10 ሰዎች መካከል 7 ገድለው ከብቶቻቸውንም ወስደዋል።

መንግስት ከታጣቂዎች ጎን እንዳለ እናምናለን የሚሉት የአካባቢው ተወላጆች፣ እስካሁን ድረስ ምን ሆናችሁዋል ብሎ አለመጠየቁ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል

የአካባቢው ተወላጆች  አንድ ነገር የማይደረግልን ከሆነ ራሳችንን ለመከላከል እንነሳለን ብለዋል።

በዛሬው እለት  ከአዲስ አበባ ወደ አፋር ክልል እና ወደ ጂቡቲ የሚያመሩ መኪኖች እንዳይንቀሳቀሱ መደረጉንና ከፍተና የሆነ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ምንጮች ገልጠዋል። መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው አስተያየት የለም።

ከአራት ቀናት በፊት በተመሳሳይ  ግጭት ከ10 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ጥቃቱን የፈጸሙት ሀይሎች በሶማሊ ክልል እና በጂቡቲ መንግስት የሚደገፉ ልዩ የኢሳ  ሀይል ታጣቂዎች መሆናቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች አሁንም በከፍተኛ ፍርሀት ውስጥ መውደቃቸውን እና ፌደራል ፖሊስ አባላት ሊከላከሉላቸው አለመቻላቸውን  መናገራቸውን መዘገባችን ይታወቃል።

የአፋር ሂውማን ራይትስ ድርጅት በክልሉ እየተፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብቶች  ጥሰት በማውገዝ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.