(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 19/2011) በአፋር ክልል የተጀመረው ተቃውሞ ቀጥሎ ዛሬ በዳሎልና ኤረብቲ አፋሮች ድምጻቸውን ማሰማታቸው ተገለጸ።
ትላንት ሰመራና በራሂሌ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በርካታ ሰዎች በልዩ ሃይል ድብደባ መጎዳታቸው ታውቋል።
በመሰንጠቅ አደጋ ውስጥ የሚገኘው የክልሉ ገዢ ፓርቲ አብዴፓ ያባረርኳቸውን አመራሮች እመልሳለሁ ሲል አስታውቋል።
ከህወሃት ጋር ግንኙነት ያላቸው ፕሬዝዳንቱ አቶ ስዩም አወል ስልጣን እለቃለሁ ቢሉም ለዘመዳቸው አውርሰው ለመልቀቅ ማቀዳቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የአፋር የስብዓዊ መብቶች ድርጅት የፌደራሉ መንግስት በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቋል።
የመከላከያ ሚኒስትሯና ኤታማዦር ሹም በአፋር የተከሰተውን ውዝግብ ተከትሎ ወደ ክልሉ ማምራታቸው ይታወሳል።
አፋሮች በስልጣን ላይ ያለው የአብዴፓ ፓርቲ አመራሮች ከስልጣን እንዲወርዱና የህወሀት ጣልቃ ገብነት እንዲቆም በመጠየቅ የጀመሩት ተቃውሞ በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ተዳርሷል።
ትላንት በሰመራ በተካሄደ ተቃውሞ በአቶ ስዩም አወል የክልሉ ፕሬዝዳንት የሚታዘዘው ልዩ ሃይል እርምጃ ወስዶ በትንሹ 10 ሰዎች ተጎድተዋል።
በበራሂሌም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ያነገቡ ነዋሪዎች አቶ ስዩም አወልና ሌሎች አመራሮች ስልጣን ለቀው ለውጡን በሚደግፉ አመራሮ እንዲተኩ ጠይቀዋል።
በዛሬው ዕለትም በዳሎልና ኤረብቲ በተባሉ ወረዳዎች የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል።
ጥያቄአችን ካልተመለሰ አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ በመስቀል አደባባይ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ተቃውሟችንን እናደርጋለን የሚሉት የአፋር ወጣቶች ፌደራል መንግስቱ የለውጥ አደናቃፊ በሆኑ የክልሉ አመራሮች ላይ ርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
በአፋር ገዢ ፓርቲ አብዴፓ ውስጥ የተፈጠረውን መሰንጠቅ ተከትሎ ወደ ክልሉ ያመሩት የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ ምን ውጤት ላይ እንደደረሱ ለማወቅ ያደርገነው ጥረት አልተሳካም።
የመከላከያ ሚኒስትሯና ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ሳዐረ መኮንን ወደ አፋር እንዳቀኑ የተነገረ ሲሆን የክልሉ ገዢ ፓርቲ አመራሮችን በተናጠል እያወያዩ እንዳለም ተገልጿል።
ስልጣኔን እለቃለሁ የሚሉት አቶ ስዩም አወል ሆኖም የሚተካቸው ሰውን እሳቸው የመረጡት መሆኑ የበለጠ ውዝግብ ሊፈጠር እንደሚችል ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።
አቶ ስዩም የጋ ዘመዳችውን ወንበሩ ላይ በማስቀመጥ በርቀት አፋር ክልልን ለመምራት ማቀዳቸው ይነገራል።
በህወሃት ልዩ ድጋፍ ያላቸው አቶ ስዩም እስከመጨረሻው ስልጣኑን ይዘው እንዲታገሉ ካልሆነም መቀሌ መተው መሸሸግ እንደሚችሉ እንደተነገራቸው ነው የኢሳት ምንጮች የሚገልጹት።
እንደሁለተኛ ክልላቸው የሚቆጥሩ ህወህቶች በደጋፊዎቻቸው አማካኝነት ማስፈራሪያ እያሰሙ ሲሆን ፌደራል መንግስቱ ጣልቃ እንዳይገባ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው። በ
ሶማሌ ክልል ጉዳይም በተመሳሳይ የፌደራል መንግስቱን ጣልቃ ገብነት ሲያውግዙ የነሩት የህወሃት ደጋፊዎች በየክልሉ የለውጥ አደናቃፊው የሆኑ አመራሮችን በገንዘብ በመያዝ ተጽዕኖ ለመፍጠር እየሞከሩ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት የአፋር ጉዳይ ወደለየለት አደጋ ውስጥ ከመግባቱ በፊት የፌደራል መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
የድርጅቱ ፕሬዝዳንት አቶ ገአስ አህመድ ለኢሳት እንደገለጹት የአፋር ጉዳይ ቀይ መስመሩን እያለፈ ነው።
ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ ትልቅ አደጋ ከማምጣቱ በፊት ግን አፋጣኝ መፍትሄ ይፈለግለት ሲሉ አሳስበዋል።