በአፋር በተከሰተው ረሃብ ዜጎች እየተሰደዱ ነው

ሐምሌ ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት ካለፈው ወር ጀምሮ ይጠበቅ የነበረው ዝናብ ባለመዝነቡ በርካታ የቀንድ ከብቶች ሲያልቁ፣ ነዋሪዎችም ቀያቸውን በመልቀቅ ምግብ ፍለጋ እየተሰደዱ ነው።ኢሳት ያነጋገራቸው ዜጎች እንደገለጹት፣ ነዋሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እንዲደርስላቸው ለመንግስት ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ እስካሁን ከመንግስትም ሆነ ከሰብአዊ መብት ድርጅቶች የቀረበላቸው ነገር የለም።
በርካታ አርብቶአደሮች ውሃና ምግብ እናገኛለን በሚል ወደ ተንዳሆ የእርሻ ልማት እየተጓዙ ነው። ወጣቶች ደግሞ በሁመራ አድርገው ወደ ሱዳን እየተሰደዱ ነው
ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንላቸው የአፋር ሰብአዊ መብት ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ገአዝ አህመድ ፣ በገዋኔ ፣ ቡሩሙዳይቱ፣ ሚሌ ፣ ጭፍራና አሳይታ አካባቢ ከፍተኛ የእንስሳት እልቂት መከሰቱን ተናግረዋል። አቶ አህመድ ከረሃቡ ጋር በተያያዘ በተነሳ የኩፍኝ በሽታ ከ40 ያላነሱ ህጻናት መሞታቸውንም ገልጸዋል።እስካሁን እርዳታ አለመድረሱንም አቶ ገአስ ገልጸዋል።
በሰሜን ሸዋ፣በዋግህምራና በወሎ በርካታ ቦታዎች ዝናብ ባለመዝነቡ ድርቅ መግባቱን ተከትሎ፣ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጉዳዩን በዝግ ስብሰባዎች ቢወያዩበትም ፣ መረጃው ወደ አደባባይ እንዳይወጣ ጥረት እያደረጉ ነው።
በግንቦት ወር በሶስተኛዉ የወሩ ሳምንት በሰ/ሸዋ ዞን 8 ወረዳዎች ማለትም በባሶናወራና፣ አንፆኪያ፣ ሲያደብር ዋዩ፣ መርሃቤቴ፣ መንዝላሎ፣ ሃገረማርያም፣ ቀወትና አንኮበር፣ እንዲሁም በደቡብ ወሎ ዞን 16 ወረዳዎች እና በደቡብ ጎንደር ዞን 6 ወረዳዎች ስርጭቱ ያልተስተካከለ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ዝናብ ያገኙ ቢሆንም ፣ ሌሎች 64 የክልሉ ወረዳዎች ዝናብ እንዳልነበራቸው ታውቆአል፡፡
በትግራይ ደግሞ ወሩ በገባ የመጀመሪያዉ ሳምንት ቆራሮና ኢሮብ ወረዳዎች ከ1-2 ቀናት ስርጭቱ ያልተስተካከለ አነስተኛ ዝናብ እንዲሁም በተምቤን፣ እንደመሆኒ፣ አህፈሮም ወረዳዎች ለውስን ቀናት ከባድ ዝናብ የነበራቸው መሆኑን ከክልሉ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ በታህታይ ኣድያቦ ወረዳ በ10 ቀበሌዎች እንደመሆኒና ኦፍላ ወረዳዎች፣ በደቡብ ምስራቅ ዞን ሳምረ ወረዳ፣ በማእከላዊ ዞን አድዋና በማይጨው ወረዳዎች፣ በተምቤን ወረዳ፣ በሰሜን ምእራብና በምእራብ ዞኖች በቆራሮ፣ አስገደ ጽምብላ፣ ጸለምቲ፣ አዲያቦ፣ እንዲሁም በአወዛጋቢዎቹ ወልቃይትና ፀገዴ ወረዳዎች ከነበረዉ አነስተኛ ዝናብ በስተቀር በአመዛኙ በቀሪዎቹ ሳምንታት የነበረዉ ዝናብ አመርቂ አለመሆኑን መረጃው አመልክቷል። በደቡብ ደግሞ በወሩ ዉስጥ በአብዛኛዉ የክልሉ አካባቢዎች ስርጭቱ የተስተካከለ ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ ዝናብ የዘነበ ሲሆን ፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም አልፎ አልፎ ከበድ ያለ ዝናብ ጥሎአል።
የክረምቱ ዝናብ ስርጭት አለመስተካከል ጋር ተያይዞ የምግብ እህል ተረጂዎች ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን ስጋት ውስጥ መውደቁን ተቀማጭነታቸው በአዲስአበባ የሆኑ ለጋሽ ሀገራትን በመትቀስ ኢሳት ሰሞኑን ዘግቧል።