ሚያዝያ ፳፭ ( ሃያ አምስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሚያዚያ 22 እስከ 23 ፣ 2009 ዓም የቀሰም ቀበና የስኳር ፕሮጀክትን የእርሻ መሬት ለማስፋት በጎሳዎች መካከል ሆን ተብሎ በተቀሰቀሰ ግጭት 23 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።
የአብሌክ አድአሊ እና ሲድሃ ቡራ ጎሳዎች በጋራ ተነስተው የመሬት ወረራውን ለመቃወም እንዳይችሉ በመካከላቸው የመከፋፈል ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ሁለቱ ጎሳዎች እርስ በርስ ሲጋጩ መከላከያዎች ምንም እርምጃ ሳይወስዱ በዝምታ መመልከታቸውንም ተናግረዋል።
በሁለቱም ወገኖች በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ግጭቱ እየሰፋ መሄዱን ተከትሎ በመጨረሻ ሰአት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጣልቃ በመግባት በጎሳ አባላቱ ላይ ተኩስ ከፍተዋል። ነዋሪዎች ከመከላከያ የተሰነዘረባቸውን ጥቃት ለመከላከል በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ 2 የመከላከያ አባላት መገደላቸውም ታውቋል።
ገዢው ፓርቲ ከዚህ ቀደም ሁለቱ ጎሳዎች በከሰል እንደተጣሉ አድርጎ ያቀረበውን ምክንያት ነዋሪዎች ተቃውመውታል። ለሸንኮራ አገዳ ተክል በሚል አርብቶአደሮቹ መሬታቸውን መቀማታቸው እንዲሁም ተባብረው ተቃውሞ እንዳያሰሙ የተለያዩ አፍራሽ ቅስቀሳዎች ሲካሄዱ ከቆዩ በሁዋላ ግጭት መነሳቱን ምንጮች አክለው ታናግረዋል።