በአፋር በተነሳ የጎሳ ግጭት ሰዎች ተገደሉ

ሚያዚያ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሃዊያ እየተባሉ በሚጠሩ የሶማሌ ጎሳዎችና በአፋሮች መካከል በተነሳ የእርስ በርስ ግጭት 6 ሰዎች መሞታቸውን በርካቶች መቁሰላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

የጠቡ መነሻ ከግጦሽ መሬት ጋር የተያያዘ ነው የሚሉት ነዋሪዎች፣ ግጭቱ ከትናንት ጀምሮ የቆመ ቢሆን ውጥረቱ ግን አሁንም እንዳለ ነው ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለትንዳሆ የሸንኮራ ምርት ማስፋፊያ በሚል ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው ተነስተው መንግስት ወደ አዘጋጀላቸው የሰፈራ ጣቢያ ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆኑ አንድ የጎሳ መሪና 6 ተከታዮቻቸው መታሰራቸው ታውቋል። ሰዎቹ የታሰሩት የዱብቲ ወረዳ አስተዳዳሪን አስደብድባችሁዋል በሚል ምክንያት ሲሆን፣ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች በበኩላቸው የደብዳቢው ማንነት ሳይታወቅ ነዋሪዎች በጅምላ ማሰሩ አግባብ አይደለም ይላሉ። አስተዳዳሪው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የተደበደቡት ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ እየዞሩ ትእዛዝ በሚሰጡበት ወቅት ነው።

በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አፋሮች ቀያቸውን ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን ኢሳት ያነጋገራቸው ሰዎች የገለጹ ሲሆን፣ ለሰፈራ ተብሎ የተዘጋጀው ቦታ ደግሞ ለኑሮ የማይስማማ ቦታ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

የአፋር ሰብአዊ መብቶች ሊቀመንበር አቶ ገአዝ አህመድ ህዝቡን ለማፈናቀል እንቅስቃሴ መጀመሩን በተመለከተ መረጃ እንደደረሳቸው ገልጸዋል።

መንግስት ህዝቡን ሲያፈናቅል ውሃ ምግብና ሌሎች መሰረታዊ ፍጆታዎችን ሳያዘጋጅ የሚያደርገው ማፈናቀል ከዘር ማጥፋት ወንጀል ተለይቶ አይታይም የሚሉት አቶ ጋአዝ የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡበት አሳስበዋል።