መጋቢት ፴( ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከ20 ሚሊዮን ያላነሱ ዜጎችን ለረሃብ አደጋ ያጋለጠው ድርቅ፣ በአፋር ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍቶአል፡፡ እናቶች በየሳምንቱ በሞትና በህይወት መካከል ያሉ ህጻናትን ይዘው ረጅም ርቅት ተጉዘው ህክምና ለማግኘት ይጥራሉ፡፡ ረሃቡ የከፋ መሆኑንና አለማቀፉ ማህበረሰብ ባይደርስ ኖሮ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል የአይ ቲ ቪ ኒውስ ጋዜጠኛ ቦታው ድረስ በመሄድ ዘግቦአል፡፡
በአንድ የህክምና ማእከል ውስጥ የሚሰራ ዶ/ር እንዳለው፣ ህጻናቱ ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ በተለያዩ በሽታዎች ተጠቅተዋል፡፡ ከ400 ሺ በላይ ህጻናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ዘጋባው አመልክቶአል፡፡
የአንድ አመቱ ህጻን ሙሃመድ እናት የሆኑት ወ/ሮ አስሊ ክሊኒኩን ለማግኘት 4 ሰአታት ያክል በእግራው ተጉዘዋል፡፡ ቤታችን ውስጥ ምንም የሚበላ ነገር የለም ይላሉ፡፡ እንስሳት አልቀዋል፤ ለህጻናቱ የሚሰጥ ወተት የለም፡፡
ሌላዋ የአንድ አመት ህጻን እናት በበኩሉዋ በምግብ እጥረት ሳቢያ ለልጁዋ ወተት ማምረት አቁማለች፤፤ እንስሳ በማለቃቸው ወተት የለም፣ ስጋ የለም፡፡ ሙሉ በሙሉ ከመንግስት በሚሰጠው ምግብ ብቻ እየኖርን ነው፡፡ ብላለች፡፡
የህጻን ሙሃመድ አብዱ እናት በበኩለዋ ያለእርዳታ ይህ አካባቢ በሙሉ መቃብር ሊሆን ይችል ነበር ብላለች፡፡ የመንግስ ሰራተኛ የሆነው የጤና ባለሙያ ሰለሞን አብርሃ ፣ ነዋሪዎቹ ወደ አካባቢያቸው በተመለሱ በ2 ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ተመሳሳይ ችግር ይገጥማቸዋል ብሎአል፡፡
ችግሩ ገና አለመቀረፉን የሚገልጸው ጋዜጠኛው፣ 1 ቢሊዮን 400 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ እርዳታ ይፈለጋል፡፡ ይሁን እንጅ አለም በተለያዩ ችግሮች በመወጠሩዋ እርዳታ ማግኘቱ ቀላል አይሆንም፡፡ ለኢትዮጵያኖች የራሃብ ወሮች፣ በተለይም ለአፋር ህዝብ እጅግ አስፈሪ ጊዜ እየመጣ ነው ጋዜጠኛ ጆን ሬይ ዘግቦአል፡፡