ግንቦት ፳፱ ( ሃያ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአፋር ክልል በጭፍራ ወረዳ ሃራ እና ሶዶማ አዋሳኝ ቀበሌዎች አካባቢ በሁለቱ ክልል ተወላጆች መሃከል በተቀሰቀሰ ግጭት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ምንጮቻችን አስታውቀዋል። በአማራ ክልል በተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ የአፋር ብሄር ተወላጆችን ከአማራ ጋር የማጋጨት ስራዎች ሆን ተብሎ በገዥው ፓርቲ አማካኝነት መፈጸሙን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ባለፈው ሶስት ወራት የመከላከያ ግቢ ውስጥ ለማስታረቅ ተብለው በመኪና ተጭነው የመጡ ስድስት የአፋር ሽማግሌዎች እና የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አብዱ ከሎይታ ተገለዋል። አቶ አብዱ ከሎይታ ቆስሎ ደሴ ሆስፒታል ውስጥ ሕይወቱ አልፏዋል። አንድ የመከላከያ ሰራዊት ወታደር መገደሉንና እስካሁን ድረስ በአማራ ተወላጆች በኩል ምን ያህል ሰው ጉዳት እንደደረሰ ማወቅ አልተቻለም። ይህ ግድያ በመከላከያ ሰራዊትና ደህንነት ሃይሎች የተቀነባበረ መሆኑንና አፋርን ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች የማጋጨት ሴራ መሆኑን የአፋር ሰብዓዊ መብት ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ገአዝ አህመድ አስታውቀዋል።
በአፋር ክልል የአባዓላ ወረዳን ወደ ትግራይ ክልል ልዩ ወረዳነት ለማጠቃለል ለሚደረገው ስራ ይረዳ ዘንድ አፋርን ከአፋር እና ከሌሎች ብሄሮች ጋር የማጋጨት ሥራዎች በመሰራት ላይ ናቸው። በዱለቻ ወረዳ ውስጥ ሁለት የአፋር ጎሳ አባላት መሃከል ግጭት በመፍጠር ከ25 በላይ ንጹሃን ዜጎች እዲገደሉ ተደርገዋል። የአፋር ክልል መስተዳደሮች ለግጭቶች መባባስ ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ። በቅርቡ በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን ድንበር ላይም ተመሳሳይ ግጭቶች ተከስተዋል። በአገር ሽማግሌዎች እና በሃይማኖት አባቶች ይድረጉ የነበሩ የእርቅ ስርዓቶችን ሆንተብለው እንዲስተጓገሉ ተደርገዋል