ኢሳት (ታህሳስ 23 ፣ 2008)
በደቡብ የአፋር አካባቢና በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን በድርቅ ምክንያት የተከሰተው የምግብ እጥረት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አርብ አስታወቀ።
በነዚህ አካባቢዎች የአደጋው አሳሳቢነት በደረጃ ሁለትና ሶስት ውስጥ ተመድቦ ቢቆይም፣ ይኸው አሃዝ ወደ ደረጃ አራት ከፍ ማለቱን የምግብ እጥረቱ የከፋ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።
በእነዚሁ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ-አደሮች አፋጣኝ የምግብ አቅርቦት ካልተደረገላቸው ችግሩ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳስቧል።
ለአስቸኳን የምግብ እጥረት የተጋለጡ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎችም በቂ እርዳታን እያገኙ እንዳልሆነ ተገልጿል።
በቀጣዮቹ ሶስት ወራቶች ውስጥም ለተረጂዎች የሚያስፈልገው እርዳታ ወደሃገሪቱ መግባት ካልጀመረ የድርቁ አደጋ በስድስት ክልሎች ውስጥ ከፍተኛ ጉዳትን ሊያስከትል እንደሚችል ድርጅቱ አክሎ አስታውቋል።
በአማራ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊያን ደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወደ 184 ወረዳዎች በደረጃ ሶስት ወስጥ ተመድበው የቅርብ ክትትል እየተደረገባቸው የሚገኝ ሲሆን፣ የበጋ ወቅቱ እየተጠናከረ በመሃሉም የድርቁ አደጋ እየተባባሰ ይሄዳል ተብሎ ተሰግቷል።
ከ 10 ሚሊዮን በላይ ደርሶ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ፈላጊዎች ቁጥርም በቀጣዮቹ ጥቂት ወራቶች ውስጥ 15 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ተተንብዮአል።
ለእነዚሁ ተረጂዎች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን የእርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውና የድርቁ አደጋ እስከቀጣዩ አመት መጋቢት ወር ድረስ የሚዘልቅ እንደሆነም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክቷል።
በድርቁ አደጋ ከቀያቸው የሚሰደዱና ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ህጻናት ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።