ኢሳት (ሰኔ 13 ፥ 2008)
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች በመሰራጨት ላይ ባለው የአጣዳፊ ትውከትና ተቅማጥ በሽታ ከ2ሺ በላይ ሰዎች ለህመም መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰኞ ገለጠ።
የአለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩዩ አካላት የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ የበሽታው ስርጭት መጨመር አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አመልክቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ በ15 ሰዎች ላይ ተከስቶ የነበረው የበሽታው ምልክት ወደ 25 የደረሰ ሲሆን፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነዋሪዎች የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ጥረት እንደሚያደርጉ በድጋሚ አሳስቧል።
ይኸው በከተማዋ በሚገኙ አስሩም ክፍለከተሞች ተሰራጭቶ የሚገኘው የአጣዳፊ ትውከትና ተቅማጥ በሽታ ወደ አጎራባች የገጠር መንደሮች ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩን የጤና ባለሙያዎች ገልጸዋል።
የበሽታው ምልክት የሚታይባቸው ነዋሪዎች ወደ መንግስትና የግል የጤና ተቋማት በመሄድ ላይ መሆናቸው በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ቁጥር በአግባቡ ለማወቅ እንዳልተቻለ ከሃገር ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
በመዲናይቱ አዲስ አበባ በመሰራጨት ላይ ያለው በሽታ በኦሮሚያ በሚገኙ ስድስት ዞኖችንና በሶማሊ ክልል በመሰራጨት ላይ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ የ19 ሰዎች ህይወት ማለፉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የበሽታው ስርጭት በታየባቸው አካባቢዎች ያለ የንጹህ ውሃ አቅርቦት እጥረት በሽታው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲዛመት አስተዋጽዖን ማድረጉንና በአፋጣኝ ርብርብ ካልተደረገ በሽታው በወረርሽን መልክ ሊቀሰቅስ ይችላል ሲሉ የህክምና ባለሙያዎች በማሳሰብ ላይ ናቸው።
በእስካሁኑ የበሽታው ስርጭት 2ሺ 145 ሰዎች ለህመም ተዳርገው እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የበሽታውን ስርጭት አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ የበሽታው ስርጭት መባባስን ተከትሎ 14 ልዩ የጤና ጣቢያዎች ተቋቁመው ታማሚዎችን እየተበቀሉ መሆኑን ገልጿል።