የካቲት ፩፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የጁመአን ስግደት ተከትሎ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ድምጻችን ይሰማ በማለት ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ ቢሞክሩም የፌደራል ፖሊስ አባላት የሀይል እርምጃ ወስደዋል።
በርካቶች መታሰራቸውን፣ መደብደባቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል::
ከፍተኛ ተቃውሞ ከታየባቸው ከተሞች መካከል ሻሸመኔ አንዱ ሲሆን፣ በርካቶች በ04 መስጊድ ተገኝተው ድምጻችን ይሰማ መሪዎቻችን ይፈቱ ማለታቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
ተመሳሳይ ተቃውሞዎች በበደሌ፣ መቱና ድሬዳዋ መካሄዳቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
የኢትዮጵያ መንግስት የሙስሊሙን ተቃውሞ ለማስቆም የተለያዩ ሙከራዎችን ቢያደርግም ተቃውሞው ከአዲስ አበባ ውጭ አድማሱን እየተስፋፋ ከመሄድ በስተቀር የመቀነስ ሁኔታ አይታይበትም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካ የሞኖሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ነገ ፌብሩዋሪ 23 በዋይት ሀውስ ፊት ለፊት ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ያደርጋሉ።
ድምፃችን ይሰማ ዋሺንግተን ዲሲ እንዳስታወቀው፤ ሰልፉ የተዘጋጀው የ ኢትዮጵያ መንግስት በሙስሊሞች ላይ እየፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማውገዝና ረዥም ጊዜ ላስቆጠረው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ትግል አጋርነትን ለመግለጽ ነው።
የ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላነሱት የመብት ጥያቄ መንግስት ቀና ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ካለመሆኑም በላይ ህግን በሚፃረር ሁኔታ በመብት ጠያቂዎቹ ላይ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን የጠቆመው ድምፃችን ይሰማ፤ ከዚያም አልፎ በሙስሊሙ መሪዎች ላይ የእስር፣የግርፋትና የማንገላታት ድርጊት መፈፀሙን አመልክቷል።
ጥቂት የማይባሉ ሙስሊሞችም በደህንነት ሀይሎች ታፍነው ተወስደው እስካሁን ያሉበት ስፍራ አለመታወቁንም ኮሚቴው በመግለጫው ጠቅሷል።
እንዲሁም ከ 1000 በላይ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ተማሪዎች በእምነታቸው ሳቢያ ከትምህርታቸው መታገዳቸውን ኮሚቴው ኢሳትን በዋቢነት በመጥቀስ በመግለጫው አስፍሯል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልም፤እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከሐምሌ 12 ጀምሮ 17 ዋነኛ የሙስሊሙን ሰላማዊ ትግል መሪዎችን ጨምሮ በርካታዎች እንደታሰሩ፣እንደተገረፉ እና እንደተሰቃዩ ሪፖርት ማውጣቱን ድምፃችን ይሰማ አስታውሷል።
ከፊል መንግስታዊ የሆኑ ተቋማትን ጨምሮ ዓለማቀፍና አገር አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የ ኢትዮጵያ መንግስት በሙስሊሞች ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍና በደል በተከታታይ ማውገዛቸውን ኮሚቴው አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞችና በእስር ላይ የሚገኙት መሪዎቻቸው በፖለቲካ ተጽጽኖ ስር ከወደቀ ፍርድ ቤት ፍትህን ሊያገኙ ይችላሉ ተብሎ ፈጽሞ እንደማይጠበቅ ዓለማቀፉ ማህበረሰብና ለጋሽ ሀገራት ሊያውቁት እንደሚገባም ድምፃችን ይሰማ ዲሲ ጠቁሟል።
በመሆኑም የ ኢትዮጵያ መንግስት በራሱ ህዝቦች ላይ እየፈጸመ ያለው የመብት ጥሰትና ወንጀል እጅግ ሳይዘገይ በዓለማቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ትኩረት ያገኝ ዘንድ ኮሚቴው ጠይቋል።
የ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ የሆኑ ወንድሞቻችንም በመንግስት የተለያዩ አፋኝ ፖሊሲዎችና አሠራሮች ተጠቂ መሆናቸውን እንደሚገነዘቡ ጠቀሰው የድምፃችን ይሰማ ዲሲ መግለጫ፤በመሆኑም ክርስቲያን ወንድሞቻቸው ነገ በዋይት ሀውስ ፊት ለፊት ሙስሊሞች በሚያካሂዱት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ አብረው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል