በአዶላ የአጋዚ ወታደሮች እርምጃ መውሰድ ጀመሩ

በአዶላ የአጋዚ ወታደሮች እርምጃ መውሰድ ጀመሩ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 30 ቀን 2010 ዓ/ም) ለሳምንት የቀጠለውን የምስራቅ ጉጂ ዞን ተቃውሞ ተከትሎ የአጋዚ ወታደሮች በህዝቡ ላይ በመተኮስ እርምጃ የወሰዱ ሲሆን፣ እስካሁን ሁለት ህጻናትን ጨምሮ 4 ሰዎች ተገድለዋል፣ በርካቶችም ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች የኦህአዴድ ባለስልጣናት አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውንና በአጋዚ ወታደሮችና በህዝቡ መካከል የሚካሄደው ፍልሚያ መቀጠሉን ተናግረዋል። ህዝቡ በድንጋይ ራሱን ለመከላከል ሲሞክር፣ አጋዚዎች ጥይት በቀጥታ በመተኮስ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል። አካባቢው ወደ ጦር ቀጠናነት መቀየሩን፣ ወጣቱ ማንኛውንም የህይወት መስዋትነት ለመክፈል ተዘጋጅቶ ትግል እያደረገ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አዲሱ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ መብቶቻቸውን የጠየቁ ዜጎች ከእንግዲህ እንደማይገደሉ ቢናገሩም፣ የዛሬው ግድያ ንግግራቸውን በአየር ላይ አስቀርቶታል።
በሻኪሶም ህዝቡ የንግድ ድርጅቶችን በመዝጋት፣ መንገዶችን በድንጋይ በመዝጋትና ምንም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይኖር በማድረግ ተቃውሞውን እየገለጸ ነው።
የተቃውሞው መነሻ ለሚድሮክ ወርቅ የተሰጠውን የ10 አመት ተጨማሪ የወርቅ ማውጣት ፈቃድ በመቃወም ቢሆንም፣ ኦሮምያ ክልልም ሆነ የፌደራሉ መንግስት እስካሁን ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ አልሰጡም። የሚድሮክ ኢትዮጵያ ባለቤት ሼክ ሙሃመድ ሁሴን አላሙዲን በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ለወራት በሳውድ አረቢያ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ።