(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 30/2010) በኦሮሚያ ክልል አዶላ ከተማ ሰላማዊ ተቃውሞ ካሰሙ ነዋሪዎች መካከል ሁለት ሰዎች መገደላቸው ተሰማ።
የከተማዋ ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን ያሰሙት በአዶላ ከወርቅ ማውጣት ጋር በተያያዘ የሜድሮክ ኢትዮጵያ ፈቃድ ታደሰ መባሉን ተከትሎ ነው።
ሜድሮክ ኢትዮጵያ በሻኪሶና በአዶላ ለ20 አመት የወርቅ ማዕድን ሲያወጣ የነበረው ስምምነት ተጠናቆ እንደገና ለ10 አመት መታደሱ በአካባቢው ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል።
ዛሬ የምስራቅ ጉጂ ዞን አካባቢዎች በአብዛኛው በተቃውሞ ውስጥ መዋላቸው ታውቋል።
ሀረቀሎ፣ አዶላ ክብረመንግስት፣ ሻኪሶ፣ ሰባ ቦሩ፣ አናሶራ፣ ኢርባሞዳና በሌታ ተቃውሞ የተካሄደባቸው ከተሞች ሲሆኑ በአዶላው የሰው ህይወት መጥፋቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ዛሬ ጠዋት በአዶላ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በመሩትና ነዋሪው በስፋት በተቀላቀለበት ተቃውሞ ሁለት ሰዎች በጥይት ተመተው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
ለህይወት አስጊ በሆነ አደጋ ውስጥ እንዳሉም ነው የኢሳት የመረጃ ምንጮች የሚገልጹት።
ከቀትር በኋላ በተደረገውና ህዝቡ በቁጣ ግልብጥ ብሎ በወጣበት ተቃውሞ የኮማንድ ፖስት ወታደሮች ሃይል በመጨመር ርምጃ ወስደው ሁለት ሰዎችን መገደላቸው ታውቋል።
ተቃውሞን ለማስቆም የወሰዱት የግድያ ርምጃ ህዝቡን ይበልጥ ያስቆጣው ሲሆን እስከምሽት ድረስ ፍጥጫ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።
ኢሳት የከተማውን ነዋሪዎች በሚያነጋግርበት ሰዓት የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበረ። ምናልባትም የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
በአዶላ ክብረመንግስት እስከምሽት ድረስ የነበረው ውጥረት ከተገደሉት ሰዎች በኋላ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን የከተማዋ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መቆሙን ለመረዳት ተችሏል።
ከአዶላ ክብረመንግስት ወደ ነጌሌ ቦረና፣ ከአዶኣላ ወደ አዲስ አበባ የሚወስዱት መንገዶች ተዘግተዋል።
ሀረቀሎ ላይ በግዙፍ እንጨቶችና ድንጋዮች መንገድ በመዘጋቱ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ መቋረጡን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች የአጋዚ ወታደሮች ህዝቡን በመደብደብ የተዘጋውን መንገድ እንዲከፈት ያደረጉት የሃይል እርምጃ ውጤት ሊያስገኝላቸው እንዳልቻለ ለኢሳት ተናግረዋል።
ትላንት ከቀትር በኋላ ተቃውሞ ረግቦባት የነበረችው ሻኪሶ ዛሬ ተቃውሞ አገርሽቶባት መዋሏ ታውቋል።
በሻኪሶና አዶላ ሱቆች፣ መደብሮች፣ ትምህርት ቤቶችና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተዘግተዋ ውለዋል።
ለሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ ተጨማሪ የ10 አመት ኮንትራት መራዘሙ ያስቆጣቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ያነሱትን ተቃውሞ በተመለከተ የህወሃት አገዛዝ ምላሽ ሰጥቷል።
ኮንትራቱ የተራዘመው የአካባቢው ጥናትና ሌሎች ምርምሮች ከተካሄዱ በኋላ በመሆኑ ሊሰረዝ አይችልም ብሏል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ ኮንትራት መራዘም ላይ ከፌደራሉ መንግስት የተለየ አቋም እንደያዘም ይነገራል።
ሆኖም ከህዝብ ጎን በመቆም የወሰደው ርምጃ ግን የለም። በምስራቅና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ነገም ተቃውሞው ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።