ሰኔ 21 ፥ 2009
በኦሮሚያ አዳማ ዙሪያ ከ80 በላይ ገበሬዎች መሬታቸው ያለካሣ ክፍያ መቀማታቸውን ተከትሎ ለክልሉ ፕሬዚደንት አቤቱታ ማቅረባቸው ተነገረ።
ገበሬዎቹ እንዳሉት የአዳማ ከተማ አስተዳደር መሬታቸውን የወሰደው ያለምንም ካሳ ድንገት በወረራ ነው።
ከመሬቱ ጋር ተያይዞ አካባቢውን እንዲለቁ ከ2002 ዓ/ም ወዲህ በመጠየቃቸው ውዝግቡ ያኔ እንደተጀመረ ገበሬዎቹ በአቤቱታቸው አስታውቀዋል።
የአዳማ አስተዳደር ለገበሬዎቹ ከ2 መቶ እስከ 5 መቶ ስኩር ሜትር ተለዋጭ ቦታ እንስጣችኋልን በሚል ቃል ቢገባም እስካሁን እንዳልተፈፀመላቸው ባቀረቡት ማመልከቻ ገልፀዋል።
መሬታቸውን ግን ለመምህራን፣ ለሲቪል ሠራተኞች እና ለኢንቨስተሮች መሰጠቱን ገበሬዎቹ ይናገራሉ።
የከተማው አስተዳደር ገበሬዎቹ ያቀረቡት አቤቱታ በማጣጣል ሕገወጦች ናቸው ማለቱን በሀገር ውስጥ የሚታተሙ ጋዜጦች ገልፀዋል። ያላቸው የመሬት ይዞታ ካርታና ሰነድም በሕገወጥ መንገድ በቀድሞ የከተማዋ አስተዳደር የተሰጣቸው መሆኑን የከንቲባው ጽ/ቤት ምክትል ቃላቀባይ ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ከተማ መሬት አስተዳደር ቢሮ ሐላፊ አቶ ምትኩ ኤሬሳ በበኩላቸው ገበሬዎቹ መሬቱን በያዙበት ጊዜ ለመንግስት ግብር አልከፈሉም የሚል ማስረጃ በመገኘቱ ካሣው እንዳልተሰጣቸው ገልፀዋል። ጉዳዩ በመጣራት ላይ ያለ መሆኑንም ሐላፊው ጨምረው ተናግረዋል። ክ80 የሚበልጡት የኦሮሚያ አርሶአደሮች ወደ አዲስ አበባ በማምራት ለኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ አቤቱታ ቢያቀርቡም እስካሁን ሰሚ እንዳላገኙም ለማወቅ ተችሏል።