በአዳማ ወረዳ በፈነዳ ቦምብ 6 ህጻናት ቆሰሉ

ኢሳት (ሰኔ 15 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል አዳማ ወረዳ ውስጥ በፈነዳ ቦምብ 6 ህጻናት መቁሰላቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ። ማክሰኞ ዕለት ከረፋዱ 4 ሰዓት አካባቢ በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ ዋቄ ሚኡ ቀበሌ ውስጥ በፈነዳት ቦምብ ሰለባ የሆኑት ዕድሚያቸው ከ 5 አመት እስከ 17 አመት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህጻናትና ታዳጊዎች መሆናቸውም ተመልክቷል።

ያረጁና የተበላሹ ብረታብረትና መሰል ነገሮችን ለሚገዙትና በተለምዶ “ቁርያሌው” በሚል ለሚጠሩት ቦምቡን እንደ ተራ ቁስ ለሽያጭ ያቀረበችውን ህጻን ጨምሮ ሶስት ሴቶች ከተጎጂዎች ውስጥ መሆናቸንም መረዳት ተችሏል። ከስድስቱ ቁስለኞች በአራቱ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑም የተገለጸ ሲሆን፣ ሁሉም ተጎጂዎች አዳማ ሆስፒታል መግባታቸው የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ አስታውቋል።

ህጻናቱ የተጎዱበት ቦምብ ኤፍ ዋን (F1) የተባለ ሲሆን፣ ቦምቡ ከቤታቸው ተገኝቷል የተባሉት የአንዲቷ ተጎጂ አባት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑንም መረዳት ተችሏል።