መጋቢት ፲፩ (አሥራ አንድ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዳማ ከተማ እና አካባቢዋ የውሃ እጥረት እና የመብራት መቆራረጥ ችግር ተባብሶ በመቀጠሉ ነዋሪዎቹ ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን አስታወቁ። አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የቀድሞው የውሃ ማጣሪያ ከከተማዋ ስፋት እና ሕዝብ ብዛት ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑን ተከትሎ የውሃ አቅርቦቱ ላይ መስተጓጎል ያስከተለ ከመሆኑን በተጨማሪ የከተማዋ አስተዳደር ንጹሕ ውሃ ለተጠቃሚዎች ለማዳረስ ምንም ዓይነት እርምጃዎችን ሲወስድ አልታየም። የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ የሆነችው አዳማ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ቀድሞው የበርሜል እና ጀሪካን ውሃ ግዢ ተገደዋል። በቤታቸው ቧንቧ እያለ ለውሃ ግዢ ከፍተኛ ወጪ የተዳረጉት ነዋሪዎች ብሶታቸውን የሚሰማቸው አካል አላገኙም።
በአዳማ ከተማ ሙስና፣ በዘመድ አዝማድ ቅጥር፣ ዘረኝነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን እነዚህን አስተዳደራዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ተግባራዊ እርምጃዎች ሲወሰዱ አይታዩም። ”የከተማዋ አዲስ ከንቲባ መሾም ከግለሰብ ለውጥ በስተቀር ለሕዝቡ መፍትሔ አላመጣም፣ ተሃድሶ የምትሉት ምንም ዓይነት ፋይዳ የለውም” ሲሉ ነዋሪዎቹ ለባለስልጣኖች ተናግረዋል።