በአዳማ እና አካባቢው የውሃ እጥረቱ ተባብሶ ቀጠለ

ጥር ፩ (አንድ)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በአዳማ ወረዳ አካባቢዎች የውሃ እጥረቱ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን ነዋሪዎቹ ለከፍተኛ ወጪና እንግልት ተዳርገዋል። በተለይ በአዳማ ናዝሬት ከተማ ውስጥ ያሉት የውሃ መስመሮች በአብዛሃኛው አገልግሎት አይሰጡም። ከዓመት በአል ዋዜማ ቀናት ጀምሮ ከተማ እና በአጎራባች ቀበሌዎች ውሃ ለማግኘት ረዥም ሰዓታት ወረፋ ለመያዝ ተገደዋል።

የከተማዋ አስተዳደር ለውሃ ችግሩ እልባት ከመስጠት ይልቅ አሁንም በአዳዲስ የሹም ሽር ሹመት ላይ ትኩረቱን አድርጓል። ከሕዝብ ብዛት ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ የውሃ ጉድጓዶች ለአካባቢው ነዋሪዎቹ ያልተሰሩላቸው ሲሆን ነባር የውሃ ጉድጓዶችን በማጽዳት እና መስመሮችን በመዘርጋት አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራዎች በክልሉም ሆነ በፌደራል መንግስት በኩል አለመሰራቱ በነዋሪዎቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ ቅሬታን ፈጥሯል።