ሰኔ ፫(ሦስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦሮምያ ክልል መስተዳድር የክልሉን የማስታወቂያ አጻጻፍ መመሪያ አልተከተሉም ያላቸውን የበርካታ ድርጅቶች ማስታወቂያዎች መሰረዙ ታውቋል።
የንግድ ማስታወቂያቸውን በአማርኛ ወይም በእንግሊዝኛ የጻፉ የንግድ ድርጅቶች ማስታወቂያቸውን እንዲለውጡና በኦሮምኛ እንዲጽፉ ሲታዘዙ ፣ ከማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ በተጨማሪ ቋንቋ ለመጻፍ የሚፈልጉ ድርጅቶች ደግሞ በኦሮምኛ የተጻፈውን በጉልህ ሁኔታ ከላይ ካስቀመጡ በሁዋላ በተጨማሪ ቋንቋ የተጻፈውን በትንሹ ከታች እንዲያስቀምጡ ታዘዋል። የመስተዳድሩ ባለስልጣናት በአማርኛ ወይም በእንግሊዝኛ ብቻ የተጻፉ ማስታወቂያዎች በቀይ ቀለም የኤክስ ምልክት በማድረግ እንዲነሱ አዘዋል።
ኦሮምኛ እና ተጨማሪ ቋንቋ አካተው የያዙ አንዳንድ ማስታወቂያዎች ኦሮምኛው ከላይ አልተቀመጠም እንዲሁም በጉልህ አልተጻፈም በሚል እንዲሰረዙ ሲደረግ፣ ማስታወቂያቸውን በኦሮምኛ ብቻ ጽፈው ሆሄያቱን በትክክል ያልጻፉ ማስታወቂያዎችም እንዲለወጡ ታዟል።
አንዳንድ ነጋዴዎች የመስተዳድሩን ድርጊት አስቂኝ ነው ብለውታል። የድርጅቶቻቸውን ማስታወቂያዎች እንዲለውጡ የታዘዙ ነጋዴዎች የመስተዳድሩን ውሳኔ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን እየገለጹ ነው።