ታህሳስ ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በትግራይ ክ/ሀገር በአዲግራት ከተማ የሙስሊሞች መቃብር ፈርሶ አጽሞች በብዛት ባንድ ጉድጓድ እንደገና እንዲቀበሩ እየተደረገ እንደሆነ ከስፍራው የደረሰን መረጃ አስረዳ።
እርምጃውን የወሰደው የከተማው አስተዳደር በቅርቡ ከተመረጡት የመጅሊስ ተወካዮች ጋር በመሆን እንደሆነ ከስፍራው ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያስረዳል።
ኢሳት ከስፍራው ያናገራቸው ሙስሊም ኢትዮጵያዊ እንደተናገሩት ከሆነ፤ ከመቃብር ስፍራው ወደ 3000 የሚጠጉ አጽሞች የሚነሱ ሲሆን፤ በስፍራው በሺሆች የሚቆጠሩ ፖሊሶች በመሰማራታቸው፤ ይሄንን እርምጃ የተቃወሙ ሙስሊሞች ወደስፍራው እንዳይደርሱ እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል።
የአካባቢው ሙስሊም ሕ/ሰብ ውሳኔውን በመቃወም ለሚመለከተው የመንግስት አስተዳደር ደብዳቤ ቢጽፍም ባለስልጣን መስሪያቤቱ ምላሽ ሳይሰጣቸው ወደርምጃው እንደገባ ያናገርናቸው አዛውንት አክለው ገልጸውልናል።
በጉዳዩ ላይ በአዲግራት ከሚገኙት ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ጋር ያደረግነውን ሙሉ ቃለምልልስ በኢሳት ሬድዮ ላይ ይከታተሉ።