ኢሳት ዜና (ሰኔ 9 ፥ 2008)
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ የተቀሰቀሰው የአጣዳፊ ተቅማትና ትውከት በሽታ በአስሩም ክፍለ ከተሞች ተሰራጨ።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በመግለጽ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ እንዲያደርጉ ሃሙስ በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል።
ወደ 15 የሚደርሱ ሰዎች በበሽታው ተይዘው በህክምና ላይ ሲሆኑ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እስካሁን ድረስ የደረሰ የሞት አደጋ አለመኖሩን ገልጿል።
የበሽታው መሰራጨት ተከትሎ አንድ ልዩ ኮማንዶ ተቋቁሞ ከአዲስ አበባ ከተማ እስከ ወረዳ ድረስ ተዋቆሮ መጠነ ሰፊ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑ ታውቋል።
በሁለት ሰዎች ላይ ባለፈው ሳምንት ታይቷል የተባለው በሽታ በአሁኑ ሰዓት በአስሩም ክፍለ ከተሞች በመሰራጨት ላይ ሲሆን በከተማዋ 14 ልዩ የማከሚያ ጣቢያዎች መቋቋማቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።
በከተማዋ የመጠጥ ውሃ እጥረት ማጋጠሙ በሽታው በአጭር ጊዜ በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች እንዲሰራጭ ማድረጉን የህክምና ባለሙያዎች አስታውቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአለም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በከተማዋ የተቀሰቀሰው በሽታ እንዲቀረፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን ሰሞኑን መግለጹ ይታወሳል።
የአጣዳፊና ተቅማትና ትውከት በሽታው በሁሉም ክፍለ ከተሞች በመሰራጨት ላይ መሆኑ በሽታው በወረርሽን መልክ ስለመከሰቱ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች አሳስበዋል።
ካልፈው ሳምንት ጀምሮ በከተማዋ የተቀሰቀሰውን የዚህኑ የበሽታ ስርጭት ተከትሎ በርካታ ነዋሪዎች ወደተለያዩ የመንግስትና የግል የህክምና ጣቢያዎች በመሄድ ላይ በመሆናቸው የታመሙ ሰዎች ቁጥርን በአግባቡ ለማወቅ እንዳስቸገረ ተነግሯል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ የበሽታውን ስርጭት በቶሎ ለመቆጣጠር የበሽታው ምልክት የታየባቸው ነዋሪዎች በአስሩም ክፍለ ከተሞች ወደ ተቋቋሙ 14 ልዩ ጣቢያዎች እንዲሄዱ ጥሪን አቅርቧል።
የአጣዳፊ ተቅማትና ትውከት በሽታ ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖች ውስጥ በመሰራጨት ላይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
ይኸው ወረርሽን በሽታ በሶማሌ ክልል ጭምር በመዛመት ላይ ሲሆን 19 ሰዎች መሞታቸውንና ወደ 2ሺ የሚጠጉ ሰዎችም በበሽታው መያዛቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ከአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታው ጎን ለጎን በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን የታይፎይድ በሽታ ወረርሽን በናዕናይና በማሊ ወረዳዎች በመሰራጨት ላይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሞኑን ይፋ አድርጓል።