ግንቦት ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአ/አ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ በዘርፉ ትምህርትና ስልጠና ለመስጠት ፈቃድ የወሰዱና በራሳቸው ምክንያት ያቋረጡ 44 የግል ኮሌጆች የመጨረሻ የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ኤጀንሲው በዛሬው እለት በመንግስታዊ መገናኛ ብዙሀን ባወጣው ማስታወቂያ የተዘጉትን 44 ያህል ኮሌጆች ዘርዝሮአል። እነዚህ ኮሌጆች ስልጠናቸውን አቋርጠው ተቋሞቻቸውን ሲዘጉ በገቡት ውልና ግዴታ መሰረት አስፈላጊ መረጃዎችንና ቁሳቁሶችን ለኤጀንሲው ማስረከብ ይጠበቅባቸው ነበር። ሆኖም ኮሌጆቹ ይህን ባለማድረጋቸው በተቋማቱ የሰለጠኑ ዜጎች መረጃዎቻቸውን ለማግኘት ከፍተኛ ውጣውረድ ገጥሞአቸዋል። ችግሩን ለመቅረፍ ይህ ማስታወቂያ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ቀርበው ንብረትና መረጃዎችን ካለስረከቡ ተቋሙን ሲመሩ የነበሩ ሀላፊዎችን በጋራና በተናጠል በህግ እንጠይቃለን ብሎአል።
ከተዘጉት ተቋማት መካከል ኩኑዝ ኮሌጅ፣ ማውንት ፉዲ ኮሌጅ፣ አወልያ ፉዲ ኮሌጅ፣ ዜጋ ቢዝነስ ኮሌጅ፣ ዳንዲቦሩ ዩኒቨርስቲና ኢንተርናሽናል ሊደርሽፕ ኮሌጅ ይገኙበታል።