ሰኔ ፲፰ (አስራ ሰምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ምንም አይነት መረጃ ወደ ውጭ እንዳይወጣ ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል የሚደረግበት ከሰኔ አንድ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን አዘጋጅነት የተጀመረው ግምገማ ፈታኝ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። ግምገማውን ተከትሎ አንዳንድ ፖሊሶች በደህንነቶች ተደብድበዋል።
በጉለሌ ክፍለከተማ መምሪያ ስር የሚገኙ አንድ የሳጅን ማእረግ ያለውና አንድ ተራ ፖሊስ የአቶ አንዳርጋቸውን ፎቶ ሞባይላቸው ላይ ተገኝቶባቸዋል እንዲሁም የግንቦት7 ደጋፊዎች ናቸው ተብለው ከተገመገሙ በሁዋላ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግባቸው ተወስኗል። ከግምገማው በሁዋላ ሳጅኑ በቀጥታ በቁጥጥር ስር ውሎ በደህንነት ሃይሎች ከፍተኛ ድብደባ እየተፈጸመበት ምርመራ ሲካሄድበት፣ ኮንስታብሉ ፖሊስ ግን በሌሎች ባልደረቦቹ ድጋፍ አምልጧል። ይህንን ተከትሎም ፖሊስ የማደኛ ትእዛዝ ከ ፎቶግራፍ ጋር በመያያዝ ሰርኩላር ደብዳቤ ቢበትንም ኮንስታብሉ ግን እስካሁን አልተያዘም።
የኮንስታብሉ ማምለጥ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓም በጉለሌ ፖሊስ መምሪያ ግምገማ ላይ የቀረበ ሲሆን፣ ግምገማውን የመራው ታጋይ ኮማንደር ወጋየሁ ወይም በቅጽል ስሙ ጦና ፣ አዲሱ ገበያ እየተባለ በሚጠራው ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ የሆነው ኮማንደር አብደላ እንዲሁም የሰው ሃይል አስተዳደር ሃላፊ ሳጅን ቢኒያም ፣ ለኮንስታብሉ መሰወር ተጠያቂዎች ናቸው በሚል በሁለቱም ላይ ጥብቅ ግምገማ እንዲደረግ ትእዛዝ አስተላልፏል። ግመገማውን ተከትሎ በሁለቱ ፖሊሶች ላይ ከባድ ቅጣት ሊጣል እንደሚችል ምንጮች ገልጸዋል።
ግምገማው ጥብቅ መሆኑን የሚናገሩት ምንጮች፣ አልተጠበቁ መረጃዎች እንዲወጡ ጫና ሲደርግና የስለላ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። ሆኖም መንግስት የተፈለገውን መረጃ እስካሁን ሊያገኝ እንዳልቻለ ምንጮች ገልጸዋል። ከምርጫ 97 ጀምሮ በአዲስ አበባ ፖሊስና በመንግስት መካከል መተማመን አይታይም። በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌንና የሌሎች ተቃዋሚ መሪዎች ፎቶዎች እንዲሁም የመብት ጥያቄዎችን የሚያቀነቅኑ ዘፈኖችን በሞባይላቸው አስቀምጠው ከተገኙ በሁዋላ፣ በመንግስት በኩል ከፍተኛ ድንጋጤ ተፈጥሯል። የአሁኑ ግምገማም ይህንኑ ተከትሎ የመጣ ነው። ግምገማው በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መካሄዱ ነው። አምና ሁሉም ፖሊሶች የፖለቲካ ስልጣና እንዲሰጣቸው ተደርጎ ነበር።
በ10 ክፍለ-ከተማዎች የሚደረገውና ሰኔ 20 የሚጠናቀቀው ግምገማ በኮሚሽን ደረጃ ፣ በሃይል መድረክ እየተባለ እንደገና ይቀጥላል።