በአዲስ አበባ የዕንቁላል ምርቶች እጥረት አጋጠመ

መስከረም ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ የዕንቁላል ምርቶች እጥረት ማጋጠሙን ተከትሎ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በአስደንጋጭ ፍጥነት እያሻቀበ መሆኑን ተጠቃሚዎች ገለጸዋል፡፡አንዳንድ አምራቾች በበኩላቸው እጥረቱ ያጋጠመው

ከመኖ እጥረት ጋር በተያያዘ ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ በተዘዋወርንባቸው ሳሪስ፣ ሾላ እና ካዛንቺስ አካባቢዎች በበርካታ መደብሮች የዕንቁላል ምርቶች ሰሞኑን ጨርሶ የሌለ ሲሆን አቅርቦቱ ባለባቸው መደብሮች የአንድ አበሻ ዕንቁላል ዋጋ ከ3 ብር ከ25 እስከ 3 ብር ከ35 ሳንቲም በመሸጥ ላይ ነው፡፡

የፈረንጅ ዕንቁላል ከብር 3 እስከ ብር 3 ብር ከ25 ሳንቲም በመሸጥ ላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል፡፡

ስለዕንቁላል ዋጋ ንረት አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት የዕንቁላል ዋጋ ባለፈው ሁለት እና ሶስት ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ መምጣቱን አስታውሰው በአሁኑ ሰዓት ያለው ዋጋ እንኳንስ አነስተኛ ገቢ ያለው በርካታ የከተማዋ ነዋሪ ቀርቶ መካከለኛ

ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ጭምር የተፈታተነ ጉዳይ ሆኖአል ሲሉ በመጥቀስ ይህ የሆነበት ምክንያት ግን እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

አንድ በዶሮ እርባታ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴ ለዚህ ዘጋቢ እንደተናገሩት የዕንቁላል ምርት እጥረት ሊያጋጥም የቻለው የመኖ አቅርቦት አነስተኛና ውድ መሆንን ተከትሎ በሥራ ላይ ያሉ አምራቾች ቀስ በቀስ ከሥራው መውጣትና አዳዲስ አምርቾች ወደዘርፉ ለመግባት

ሳቢ ሁኔታ አለመኖሩ ዋንኛ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ምርቱ ላይ ያለው ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው ይህም ሆኖ እንኳን አምራቹን ተጠቃሚ የሆነበት ሁኔታ ባለመኖሩ ብዙዎቹ ከዘርፉ እየወጡ ነው፡፡ መንግስትም ችግሩን ቢያውቅም

ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዱ ችግሩን አባብሶታል ብለዋል፡፡