ኢሳት (ሃምሌ 21 ፥ 2008)
በአዲስ አበባ ከተማ በመስፋፋት ላይ ያለውን የኮሌራ በሽታ ስርጭት ተከትሎ በመዲናይቱ የንጽህና ጉድለት ታይቶባቸዋል የተባሉ ከ800 በላይ የምግብና የመጠጥ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተዘጉ።
የከተማዋ የጤና ቢሮ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባካሄደው ዘመቻ በታሸጉት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ በርካታ ሰራተኞች በበሽታው ተይዘው መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ገልጿል።
ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የተቀሰቀሰው ይኸው በሽታ አሁንም ድረስ በመሰራጨት ላይ ሲሆን በርካታ ነዋሪዎች ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት በመሄድ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
በከተማዋ ያለው የንጽህና መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የንጽህና መጓደል ለበሽታው መሰራጨት ምክንያት መሆኑን የጤና ባለሙያዎች በመግለጽ ላይ ቢሆንም የከተማው የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የውሃ እጥረቱን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በኩል አስታውቋል።
እንዲዘጉ እርምጃ ከተወሰደባቸው ከ800 በላይ ምግብ ቤቶችና የመጠት አገልግሎት መስጫ ተቋማት በተጨማሪ ተመሳሳይይ ችግር ታይቶባቸዋል የተባሉ ከ4ሺ በላይ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ለመረዳት ተችሏል።
በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ሲሰሩ የነበሩና በኮሌራ በሽታ የተያዙ ሰዎች የህክምና አገልግሎት እየተደረገላቸው ሲሆነ ከ2ሺ የሚበልጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በኮሌራ ወረርሽኝ በህመም መዳረጋቸው ተገልጿል።
የጉድጓድና የምንጭ ውሃን መጠቀም እንዲሁም በምግብ ቤቶች ንጽህናቸው ያልተጠበቁ ምግቦችንና የመጠጥ ውሃዎች ለተጠቃሚዎች መቅረባቸው ለበሽታው ስርጭት ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ አሸናፊ ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
በመባባስ ላይ ባለው በዚሁ በሽታ እስካሁን ድረስ በመዲናይቱ በትንሹ ስድስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ በኦሮሚያና በሶማሊ ክልል በሽታው በመሰራጨት ላይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ የመለክታል።
በሃገሪቱ በመጣል ላይ ያለው ዝናብ የበሽታውን ስርጭት ያባብሰዋል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን፣ የከተማዋ ጤና ቢሮ ነዋሪዎች ውሃን በማፍላት ብቻ እንዲጠቀሙ አሳስቧል።
ይሁንና፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በበሽታው ስርጭት የደረሰን አጠቃላይ ጉዳት ለህዝብ መግለጹ በነዋሪው ዘንድ ፍርሃትን ያሳድራል በማለት በበሽታው የሞቱ ሰዎችን በትክልል ከመግለጽ ተቆጥቧል።