በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ከሶስት ሺ በላይ መኖሪያ ቤቶች ለመልሶ ማልማት ፕሮጄክት ሊፈርሱ መሆኑ ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 5 ፥2009)

ክፍለ ከተማው የመኖሪያ ቤቶቹን ለማፍረስ በቅርቡ የተዋወቀው 10ኛው የከተማዋ የተሻሻለ የማስተር ፕላን በከተማው አስተዳደር መጽደቁን እየተጠበቀ የሚገኝ ሲሆን፣ እንዲፈርሱ የተወሰነባቸው 3ሺ 221 መኖሪያ ቤቶች ከ12 አመት በፊት የተገነቡ መሆናቸውን አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል። የተወሰኑ መኖሪያ ቤቶች ከ20 አመት በፊት የተገነቡ መሆናቸው ታውቋል።

የየካ ክፍለ ከተማ እንዲፈርሱ በተወሰነባቸው አካባቢዎች የከተማ አስተዳደር የመልሶ ማልማት ፕሮጄክቶችን ለማካሄድ እቅድ እንዳለው ገልጿል።

ከ3ሺ 221ዱ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ  እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2005 አም የተገነቡ 660 መኖሪያ ቤቶች የሚገኙ ሲሆን፣ መኖሪያ ቤቶቹ ህጋዊ ባለመሆናቸው እጣ ፈንታቸው አለመታወቁን የከተማዋ አስተዳደር የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ ቃል አቀባይ አቶ ንጉሱ ተሾመ ለጋዜጣው ገልጸዋል። ይሁንና አብዛኛው እንዲፈርሱ የተወሰነባቸው ቤቶች 75 ስኩዌር ሜትር ምትክ ቦታ የተሰጣቸው ሲሆን፣ 660 መኖሪያ ቤቶች በምትክ ቦታው ሳይካተቱ ቀርቷል።

የከተማዋ አስተዳደር በቅርቡ ተሻሽሎ የቀረበን ማስተር ፕላን ያጸድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህንኑ ተከትሎ ከ3ሺ የሚበልጡ የመኖሪያ ቤቶቹን የማፍረስ ዕርምጃ እንደሚካሄድ የየካ ክፍለ ከተማ ሃላፊዎች አስታውቀዋል።

ይሁንና አስተዳደሩ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2005 በኋላ የተገነቡ መኖሪያ ቤቶችን በህገ-ወጥ የሚመለከት በመሆኑ በርካታ ሰዎች የሚገቡበትን እንደማያውቁና ስጋት አድሮባቸው እንደሚገኝ ተመልክቷል። በክፍለ ከተማ ምትክ ቦታቸው ያልተረከቡ ነዋሪዎች እስከተያዘው ወር መጨረሻ ድረስ እንዲወስድ አሳስቧል።

የከተማዋ አስተዳደር ለመልሶ ግንባታና ልማት በሚል ስም ለአመታት ሲያካሄድ የቆየው የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረስ ዕርምጃ በነዋሪዎች ዘንድ ተቃውሞ ሲያስተናግድ መቆየቱ ይታወሳል።

ነዋሪዎች የሚሰጣቸው ምትክ ቦታ አነስተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ ስፍራው ከከተማ የራቀና መሰረተ-ልማት ያልተሟላለት እንደሆነ ይገልጻሉ። ህጋዊ አይደላችሁም ተብለው ለበርካታ አመታት ከኖሩበት የተፈናቀሉ ሰዎች በበኩላቸው ይዞታቸውን ያለምትክ ቦታና መጠለያ አንለቅም በማለታቸው ከጸጥታ ሃይልች ጋር መጋጨታቸውን የሰው ህይወት ማለፉም የሚታወስ ነው።